​የጣና ሞገዶቹ ተጨማሪ ረዳት አሠልጣኝ ሾሙ

የአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ውል ያራዘሙት ባህር ዳር ከተማዎች ሁለተኛ ረዳት አሠልጣኝ ሾመዋል።

ከወራት በፊት የዋና አሠልጣኛቸው ፋሲል ተካልኝን ውል ለሁለት ዓመታት ያራዘሙት ባህር ዳር ከተማዎች በ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ አዳዲስ ተጫዋቾቸን ወደ ክለባቸው በመቀላቀል ዝግጅታቸውን በባህር ዳር እየከወኑ ይገኛሉ። ምንም እንኳን ቡድኑ ከሳምንታት በፊት ዝግጅቱን ዓባይ ምንጭ ሎጅ መቀመጫውን በማድረግ ቢጀምርም የዋና አሠልጣኙ ረዳቶች ሳይታወቁ ቀርተዋል። ይህንን ተከትሎም ዋና አሠልጣኙ ዓምና የነበረው የአሠልጣኝ ቡድን አባላት እንደሚቀጥሉ በማሳወቁ ረዳት አሠልጣኝ ታደሰ ጥላሁን እና የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ አሻግሬ አድማሱ እንዲቀጥሉ ሆኗል።

ከሁለቱ ረዳቶች በተጨማሪ አሠልጣኝ አብርሃም መላኩ የአሠልጣኝ ቡድኑን ተቀለቅሏል። ከ2004 – 2010 በአውሥኮድ በምክትል እና በዋና አሠልጣኝነት የሠራው አብርሃም በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የእግርኳስ ስልጠና ትምህርቱን እየተከታተለ በከተማው ፍኖተ ጣና የእግርኳስ አካዳሚ የሚል የታዳጊዎች ማጎልበቻ አካዳሚ በመክፈት ሲያሰራ ቆይቷል። ዓምና ደግሞ አዲስ የተቋቋመውን የባህር ዳር ከተማ የተስፋ ቡድን በዋና አሠልጣኝነት በመያዝ ግልጋሎትን ሲሰጥ ቆይቷል። ዘንድሮ ደግሞ ውሉን ካራዘመው አሠልጣኝ ታደሠ ጋር በመሆን ፋሲል ተካልኝን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ለመርዳት ፊርማውን አኑሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ