በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመሩ በርካታ ዝውውሮችን ከፈፀሙ በኋላ ከነባሮቹ ጋር በማቀናጀት ያለፉትን ሳምንታት በሆሳዕና ከተማ ቅድመ ዝግጅታቸውን እየሰሩ የሚገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች ሁለት የውጪ ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች ወደ ክለቡ አምጥተዋል።
የመጀመሪያው ፈራሚ ከአራት ዓመታት በኃላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው አይዛክ ኢሴንዴ ነው፡፡ የሀገሩን ክለብ ቪክቶርን ለቆ ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመቀላቀል በክለቡ አምስት ዓመታት አስደናቂ ብቃቱን ሲያሳይ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠርቶ መጫወት የቻለው አይዛክ ፈረሰኞቹን ከለቀቀ በኃላ ወደ ዛምቢያ አምርቶ በቢውልድኮን፣ በሀገሩ ክለብ ቡሶጋ ዩናይትድ እንዲሁም ያለፈውን ዓመት በህንዱ ትራሁ ክለብ ተጫውቶ ካሳለፈ በኃላ ሀድያ ሆሳዕናን ተቀላቅሏል፡፡
ሌላኛው ፈራሚ ጋናዊው ተከላካይ ሊ አዲ ነው፡፡ በእግርኳስ ህይወቱ በአስራ አንድ ክለቦች ውስጥ መጫወት የቻለው ይህ የ30 ዓመት ተጫዋች ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በክለብ ደረጃ ያለፉትን አራት ዓመታት በዛምቢያው ሉሳካ ዳይናሞስ እና በደቡብ አፍሪካው ፍሪ ስቴትስ ቆይታ ካደረገ በኃላ ሀድያ ሆሳዕናን ተቀላቅሏል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ