​አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ለአንድ ተጫዋች ጥሪ አቀረበ

በአሁኑ ሰዓት የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአንድ አዲስ ተጫዋች በዛሬው ዕለት ጥሪ አድርጓል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ባለፈው ሰኞ ቡድኑ ወደ ታንዛነያ ሊያመራ ሲል አንድ ግብ ጠባቂ የኮቪድ 19 የተገኘበት በመሆኑ እና እንዲሁም አማካዩ ዳዊት ታደሰ በድጋሚ መመርመር አለበት በመባሉ ወደ ስፍራ አላቀኑም ነበር፡፡ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናም የኮቪድ 19 በተገኘበት ተጫዋች ምትክ ከ2009 ጀምሮ ከሀዋሳ ከ17 እና 20 ዓመት በታች እንዲሁም በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም የተጫወተው ግብ ጠባቂ ምንተስኖት ጊምቦን የጠሩ ሲሆን ተጫዋቹም የኮቪድ 19 ተመርምሮ ነፃ በመባሉ ሌላኛው ከሀዋሳ ተመርጦ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ዝግጅት ሲያደርግ ሰንብቶ ሳይጓዝ የቀረው እና በተመሳሳይ ነፃ የተባለው ዳዊት ታደሰም ወደ ታንዛኒያ በመጓዝ ቡድኑን የሚቀላቀሉ ይሆናል፡፡

ከሴካፋ ጋር በተያያዘ መረጃ ትናንት ውድድሩ በምድብ 1 አስተናጋጇ ታንዛኒያ በብላክ ሪኖ አካዳሚ ስታዲየም የጅቡቲ አቻዋን አስተናግዳ ስድስት ለዜሮ በሆነ ድል ረታ ውድድሩን በድል ጀምራለች፡፡ ይህ የመክፈቻ ጨዋታንም ኢትዮጵያዊያኑ ዳኞች ትግል ግዛው በረዳትነት በላይ ታደሰ በአራተኛ ዳኝነት መርተውታል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ