በአሠልጣኝ ደጋዓረገ ይግዛው የሚመሩት ወልቂጤ ከተማዎች ከበርካታ ወራት በፊት ቃል የተገባላቸው ሽልማት ዛሬ ተበርክቶላቸዋል።
የ2011 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድርን በምድብ ለ ተመድቦ ሲያከናውን የነበረው ወልቂጤ ከተማ 46 ነጥቦች በመያዝ ወደ ዋናው የሀገሪቱ የሊግ እርከን ማደጉ ይታወሳል። ክለቡ በጊዜው ያሳካውን ድል ተከትሎም የደቡብ ክልል የክለቡን አባላት የሚያጓጉዝ አውቶቡስ ለመሸለም ቃል ገብቶ ነበር። ክልሉ በወቅቱ የገባውን ቃል ዓምና ባይፈፅምም በዛሬው ዕለት የተገባው ቃል መፈፀሙ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።
ከአውቶቡሱ በተጨማሪ ክልሉ 100 ሺ ብር ለክለቡ ተጫዋቾች ለመስጠት ቃል ሰጥቶ እንደነበረ አይዘነጋም። እንደ አውቶብሱ ክልሉ ይህንን ቃል የገባውን ገንዘብ ዛሬ ለክለቡ ለማስረከብ የፈቀደ ቢሆንም ክለቡ ቃል የተገባለትን ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሰጥለት መወሰኑ ተሰምቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ