​ፋሲል ከነማ የመልስ ጨዋታውን የት ያደርግ ይሆን?

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚሳተፈው ፋሲል ከነማ የመጀመርያ ጨዋታውን ከሜዳ ውጭ ለማድረግ ዛሬ አመሻሹ ላይ ጉዞውን ቢያደርግም የመልሱን ጨዋታ የት እንደሚያከናውን አጠያያቂ ሆኗል።

በአፍሪካ መድረክ በኮፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክለው ፋሲል ከነማ ከቱኒዚያው ዩ ኤስ ሞናስቲር ጋር መደልደሉ ይታወቃል። የመጀመርያ ጨዋታውንም ከኅዳር ከ18-20 ባሉት ቀናት ከሜዳው ውጪ ለማድረግ ለሳምንታት ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ አመሻሹ ላይ ወደ ስፍራው የሚያቀና ይሆናል። የመልሱን ጨዋታ በሳምንቱ በሜዳው በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚያደርግ አስቀድሞ መርሐግብር መውጣቱም ይታወሳል።

ሆኖም አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ አንፃር የሚጫወትበት ሜዳ እንደ ብሔራዊ ቡድኑ ሁሉ ፋሲል ከነማ የሜዳ ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችል ፍንጮች እየወጡ ይገኛል። ምንም እንኳን ከክለቡ በኩሉ የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም ምን አልባትም ጨዋታውን አዲስ አበበ ስታዲየም ለማድረግ እንደታሰበ ሰምተናል። ወደፊት በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎች ካሉ ተከታትለን የምናቀርብ መሆናችን ከወዲሁ የምንገልፅ ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ