ከፍተኛ ጭቅጭቅ ያስነሳው የሜዳ መረጣ ጉዳይ በመጨረሻም በዕጣ ተለይቷል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ2013 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድርን የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት እና የደንብ ውይይት ከደቂቃዎች በፊት አከናውኗል። የውድድሩ ደንብ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ባለበት ሰዓትም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ውድድሮቹ የት እንደሚካሄዱ ተናግረዋል። በዚህ ሰዓት አንዳንድ ተሳታፊ ክለቦች የሜዳ መረጣው ላይ ከፍተኛ ቅሬታ በማስነሳታቸው ሜዳዎቹ በዕጣ እንዲለዩ ሆኗል። ነገርግን ምድብ አንድ ላይ የተደለደሉት አብዛኞቹ ክለቦች የሰሜን እና የአዲስ አበባ ክለቦች በመሆናቸው እነሱ የሚጫወቱበት ሜዳ ያለዕጣ ባቱ ስታዲየም ላይ እንዲሆን ተወስኗል።
ነገርግን ምድብ ሁለት እና ሦስት ላይ ያሉ ክለቦች ከፌዴሬሽኑ እንዲጫወቱበት የቀረበውን ስታዲየም መቀበል ሳይችሉ በስብሰባ አዳራሹ ከፍተኛ ጭቅጭቅ ተነስቷል። ይህንን ተከትሎ የመጫወቻ ሜዳዎቹ በዕጣ እንዲለዩ ሆኗል። በወጣው ዕጣ መሠረትም ምድብ ሁለት ላይ የሚገኙት ክለቦች የመጀመሪያ ዙር ውድድራቸውን ሀዋሳ ላይ እንዲያካሂዱ ሆኗል። ምድብ ሦስት ላይ ያሉ ክለቦች ደግሞ ውድድራቸውን ጅማ ስታዲየም ላይ እንዲከውኑ ተወስኗል።
የመጀመሪያው ዙር ውድድር በሦስቱ ከተሞች ከተደረገ በኋላ ደግሞ የሁለተኛው ዙር ውድድር በአዳማ፣ ሶዶ እና ነቀምት ስታዲየሞች እንዲደረጉ መወሰኑ ተረጋግጧል።
የውድድር ስታዲየሞቹን ከእግርኳስ ፌዴሬሽኑ እና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከመጡ ባለሙያዎች የተወጣጣ ልዑካን ከወራት በፊት እንዲለዩ መደረጉም ተገልጿል።
© ሶከር ኢትዮጵያ