ከፍተኛ ሊግ | ደቡብ ፖሊስ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

ላለፉት ሁለት ዓመታት በረዳት አሰልጣኝነት ሲሰራ የነበረው አላዛር መለሰ ደቡብ ፖሊስን በዋና አሰልጣኝነት ተረክቧል፡፡

ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር የአንድ አመት ቀሪ ውል ቢኖረውም ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሳልፎ የሰጠው ክለቡ አዲስ የሾመው አላዛር መለሰን ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በረዳት አሰልጣኝነት የሰራ ሲሆን ከ2009 በፊት ባሉት ዓመታት ክለቡን ለቆ ታዳጊ ተጫዋቾች ላይ አሰልጣኙ ሲሰራ ቆይቷል። ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ ወደ ደቡብ ፖሊስ ተመልሶ በረዳት አሰልጣኝነት አገልግሏል፡፡ በተለይ ክለቡ ከስምንት ዓመት በኋላ 2011 በፕሪምየር ሊጉ ሲሳተፍ ክለቡን ለሁለት ጨዋታዎች መርቶ አመርቂ ውጤትን በወቅቱ ያመጣ ሲሆን የተሰረዘውንም የውድድር ዓመት ክለቡን በረዳትነት ካገለገለ በኋላ ዘንድሮ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመራ ሀላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

የደቡብ ፖሊስ እግር ኳስ ክለብ አዳዲስ ተጫዋቾች ለማስፈረም የሙከራ ዕድልን ሰጥቶ እየተመለከተ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡ አጠናቆ ወደ ልምምድ እንደሚገባም ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ