ወላይታ ድቻ በሦስት ተጫዋቾቹ ክስ ሲቀርብበት ተጫዋቾቹ ለሁለተኛ ጊዜ ልምምድ አቁመዋል

ወላይታ ድቻ በሦስት የክለቡ ተጫዋቾችን አቤቱታ የቀረበበት ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ የአምስት ወር ደመወዛችን በተባለው ቀን አልተከፈለንም በሚል የክለቡ አባላት ልምምድ አቁመዋል፡፡

ክለቡ ለዘንድሮው የ2013 የውድድር አመት ለፕሪምየር ሊጉ ዝግጅት ማድረግ ከጀመረ ወራት ሊቆጠሩ ጥቂት ቀናት ቀርተውታል፡፡ ይሁንና የክለቡ ተጫዋቾች ከሀምሌ ወር ጀምሮ እስከ ያዝነው ወር ድረስ ደመወዝ አልተከፈለንም በማለት ኅዳር ወር አጋማሽ ላይ ልምምድ ማቆማቸውን በወቅቱ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ እያሱ ነጋም በጊዜው በቶሎ ክፍያውን እንደሚፈፅሙ ገልፀው ተጫዋቾቹ ወደ ልምምድ ባቆሙ በአራተኛ ቀን ዳግም ልምምድ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡ ሆኖም ክለቡ አሁንም ባለው ቃል አልተገኘልንም በማለት የክለቡ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ከትናንት ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ ልምምድ ማቆማቸውን ተጫዋቾቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ተጫዋቾቹ እንደገለፁት ከሆነ “በተደጋጋሚ እየጠየቅን ቀን እየተቆረጠ በዚህ ቀን ይሰጣችዋል እያሉ መፍትሄ ሳይገኝ ቀናቶች ሄዱ። ለዚህም የራሳችንን ውሳኔ ለመወሰን ተገደናል። ማቆማችንን ተመልክቶ መጥቶ ያነጋገረን ሀላፊም የለም። ” ብለዋል።

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ እያሱ ነጋ ጉዳዩ ከበጀት ጋር የተያያዘ በመሆኑ መቸገራቸውን በምላሻቸው የነገሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክፈል በጥረት ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል። ለተጫዋቾቹም ትዕግስት እንጂ ልምምድ ማቆም መፍትሄ አይሆንም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ሦስት ተጫዋቾች ክለቡን ከሰዋል። በተሰረዘው የውድድር ዓመት አጋማሽ ላይ ለክለቡ ፊርማቸውን አኑረው የነበሩት አማካዩ ሚካኤል ለማ፣ ተከላካዩ አበባው ቡጣቆ እና አንጋፋው አጥቂ መሐመድ ናስር “ቀሪ የስድስት ወር ውል እያለን ክለቡ አሰናብቶናል። የጠየቅነውንም ጥያቄ በአግባቡ አልመለሰለንም። በገባነው ውል መሠረት ደመወዛችንን ከፍሎ ያሰናብተን ብለን ክለቡን ስንጠይቅ መልስ ማግኘት ባለመቻላችን ለፌዴሬሽኑ የቅሬታ ደብዳቤን አስገብተናል።” ሲሉ ነግረውናል። የክለቡ ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው ” ምንም አይነት ክስ በፌዴሬሽኑ በኩል ወደ እኛ አልመጣም። ተጫዋቾቹ ከመክሰስ እና ከመጥፋት ይልቅ ወደ ክለቡ ቀርበው መፍትሔ ማበጀት አለባቸው እኛ አንከፍልም አላልንም። ተጫዋቾቹ ወደ ክለቡ መጥተው ጉዳያቸው መጨረስ ይችላሉ። ከቡድኑ የተቀነሱት ግን አሰልጣኙ አልፈልጋቸውም ስላለን ነው።” ብለዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ