በአዲስ አበባ ሊደረግ የነበረው የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ ተሰርዟል

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ለማድረግ ቀጠሮ ቢይዝም ሃሳቡን መቀየሩ ታውቋል።

በአሁኑ ሰዓት በፊፋ የአምስት ዓመት ዕግድ ተጥሎባቸው የነበረው የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ትራንዚት ሲያደርጉ ኢትዮጵያ የካፍን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ እንድታስተናግድ መመረጧን ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ገልፀው እንደነበር ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ከታኅሣሥ 1-10 ድረስ በአዲስ አበባ ይደረጋል ተብሎ ይታሰበውን ይህን ጠቅላላ ጉባኤ ለማስተናገድ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ሥራዎችን እየከወነ ቢገኝም ጉባኤው አዲስ አበባ ላይ እንደማይደረግ ተገልጿል።

የካፍ ኢመርጀንሲ ኮሚቴ እንደገለፀው ከሆነ ተቋሙ ይህንን ውሳኔ የወሰነው በሜዲካል ኮሚቴው በቀረበለት ምክረ ሃሳብ እንደሆነ አስረድቷል። በተለይም በአህጉሪቱ ያለውን የኮቪድ-19 ስርጭት ታሳቢ በማድረግ ጉባዔውን በአካል በመገናኘት ማከናወን አስጊ እንደሆነ በማሰብ ውሳኔው መወሰኑ ተብራርቷል። ከኮቪድ በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታም እንደ ተጨማሪ ምክንያትነት እንደተያዘ ተጠቁሟል። ይህንን ተከትሎ ፊፋ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን እንዳከናወነው ካፍም ጉባኤውን በቪዲዮ ኮንፍረንስ ለማከናወን ወስኗል።

© ሶከር ኢትዮጵያ