የከፍተኛ ሊግ ውድድር የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ዛሬ ተከናውኗል

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር የ2013 ዓመት የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ዛሬ ሲያከናውን የደንብ ውይይትም ተደርጓል።

ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው በዚህ መርሐ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ዓሊሚራህ መሐመድ፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዲሁም በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦች ተገኝተዋል። በቅድሚያም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የመክፈቻ ንግግር በማድረስ መድረኩን ከፍተዋል።

“ዓምና ውድድሩ ሲሰረዝ መሪ የነበሩ ክለቦች እነሱ ላይ ብቻ የተደረገ ነገር እንደሆነ አድርገው በየሚዲያው ስያወሩ ነበር። እኛ ማንንም ለመጥቀምም ሆነ ለመጉዳት አደለም ያንን የሰራነው። በወረርሽኙ ምክንያት ነው። ዓለም ላይ በመጣ ወረርሽኝ እኛ መሰደብ የለብንም። እናንተስ በእኛ ቦታ ብትሆኑ ምን ነበር የምታደርጉት። ስለዚህ ዓምና በተፈጠረው ነገር እኛ መወቀስ የለብንም።”

ፕሬዝዳንቱ ዓምና የተፈጠረውን ነገር ተንተርሰው ሃሳባቸውን ካጋሩ በኋላ ክለቦች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበው ውድድሩ በተመረጡ ቦታዎች ላይ መደረጉን ለክለቦቹ የተሻለ ነገር መሆኑን አውስተዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ላይ የውጪ ተጫዋቾች አይኖሩም። ስለዚህ ከአሁኑ ጀምሮ ይህንን ጉዳይ አስቡበት።” የሚል አጭር ትዕዛዝ አዘል መልዕክት ለክለቦች አቅርበዋል።

በንግግራቸው መገባደጃ ላይም ሊጉን እንደ ፕሪምየር ሊጉ ለመሸጥ ክለቦች የተሻላቸውን እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል። በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የትጥቅ አቅራቢ ተቋም (UMBRO) ጋር በመነጋገር ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ኳሶችን እና የጨዋታ ዳኞችን ትጥቅ ለማቅረብ መዘጋጀቱን አብስረዋል።

ከአቶ ኢሳይያስ የመክፈቻ ንግግር በኋላ የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኃይሉ ምረትአየሁ የ2013 የውድድር ደንብን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል። በቀረበው ደንብ ላይ ብዙም የተለዩ ነገሮች ባይሰሙም ከዓምናው ችግር ተነስቶ በውድድሩ ላይ የተካተተውን የ50+1 ህግ አቶ ኃይሉ በደንብ አስረድተዋል። በዚህም ውድድሩ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቋረጡ ከሆነ ነገርግን ጨዋታዎቹ 50+1 (ከግማሽ በላይ) ተደርገው ከሆነ አሸናፊዎች እና ወራጆች በጊዜው ያለውን ሰንጠረዥ ታሳቢ በማድረግ እንደሚለዩ ገልፀዋል።

ከ30 ደቂቃ ባልዘለለ ጊዜ ውስጥ ደንቡ ከቀረበ በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የህክምና ኮሚቴ አባል ዶ/ር ቃልኪዳን ዘገየ ክለቦች በውድድሩ ሊከተሏቸው የሚገባውን የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል። በገለፃቸውም በርከት ያሉ አንኳር ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን በአጽንኦት ደግሞ ክለቦች የኮቪድ-19 ኦፊሰር እንዲቀጥሩ ተናግረዋል። በተጨማሪም ከጨዋታ በፊት የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያደርጉ እና መቀመጫቸውን በሚያደርጉበት ቦታ የማግለያ ቦታ እንዲያዘጋጁ ተናግረዋል።

ከዶክተሯ ንግግር በኋላ የፌዴሬሽኑ የዳኞች ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ መኮንን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ዳኞች እና ታዛቢዎች ማኅበር የመጡት አቶ ሚካኤሌ የዳኞችን ዝግጁነት እና አዳዲስ የጨዋታ ህጎችን አብራርተዋል። አቶ ሚካኤል በበኩላቸው ከላይ የተጠቀሱትን ካነሱ በኋላ ፌዴሬሽኑ ዳኞች የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ የሚጥርበትን መንገድ አድንቀዋል። ከምንም በላይ ደግሞ ዓምና ሊጉ ተቋርጦ ዳኞች እንዳይቸገሩ ፌዴሬሽኑ ያደረገውን ጥረት አሞካሽተዋል። በተጨማሪም ለዳኞች ትጥቅ እንዲዘጋጅ በመደረጉ ምስጋና አቅርበዋል።

ከመድረኩ የተለያዩ ገለፃዎች ከተደረጉ በኋላ ቀደም ብሎ የቀረበው ደንብ ላይ ውይይት እንዲደረግ አቶ ኢሳይያስ ጂራ መድረኩን ክፍት አድርገው ውይይቶች መምራት ጀምረዋል። በዚህ የውይይት ጊዜም ክለቦች ከምድብ አደላደል ጋር፣ ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን እንዲራዘም ከመፈለግ ጋር እንዲሁም ከመጫዎቻ ሜዳዎች ጋር የተያያዙ አስተያየት እና ጥያቄዎችን ለፌዴሬሽኑ እና ለውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴው አቅርበዋል። በቀረቡት ጥያቄዎች ላይም መድረኩ የተለያዩ ምላሾችን ሰጥቷል።

አቶ ኢሳይያስ ምላሾችን ከመስጠታቸው በፊትም ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ለስፖርት ቤተሰቡ መረጃዎች በአግባቡ እንዲደርሱ የሚያደርገውን ሶከር ኢትዮጵያን ታዳሚው በጭብጨባ እንዲያመሰግን ጠይቀው ለድህረ-ገፃችን ከፍተኛ ምስጋና ተችሯል። ከዛም የ2013 የከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር በባቱ፣ ሀዋሳ እና ጅማ ስታዲየም እንዲደረግ መወሰኑን ተናግረዋል። የሁለተኛ ዙር ውድድሩ ደግሞ አዳማ፣ ሶዶ እና ነቀምት ስታዲየሞች ላይ እንዲደረግ የመጨረሻ ቃል ተሰጥቷል። በተመረጡት ከተሞችም ለክለቦች የሚበቁ የመለማመጃ ሜዳዎች እንደሚኖሩ መረጋገጡም ተያይዞ ተነግሯል። ከምድብ አደላደል ጋር በተያያዘም ክለቦች የሚገኙበትን ርቀት ታሳቢ ተደርጎ ምድቦቹ መሰራታቸውም ተብራርቷል። እርግጥ የምድብ አደላደሉ በዕጣ ይሁን የሚል ሀሳብ ከታዳሚያኑ ተነስቶ በአብላጫ ድምፅ ፌዴሬሽኑ ያወጣው ምድብ ፀድቋል።

ለጥያቄዎቹ ምላሾች ከተሰጡ በኋላም በቀጥታ ወደ ዕጣ አወጣት መርሐ-ግብሩ ተኬዷል።

በዚህም መሰረት ምድብ ሀ ላይ

1 ሰ/ሸ ደብረብርሃን
2 ደደቢት
3 ለገጣፎ ለገዳዲ
4 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
5 ፌዴራል ፖሊስ
6 ወልዲያ
7 ደሴ ከተማ
8 ወሎ ኮምቦልቻ
9 መከላከያ
10 ገላን ከተማ
11 ሶሎዳ አድዋ
12 አክሱም ከተማ

ምድብ ለ

1 ጅማ አባቡና
2 ነቀምት ከተማ
3 አዲስ አበባ ከተማ
4 ሀምበሪቾ ዱራሜ
5 ሻሸመኔ ከተማ
6 ጋሞ ጨንቻ
7 ኢኮስኮ
8 ቤንች ማጂ ቡና
9 ወላይታ ሶዶ
10 ከፋ ቡና
11 አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ
12 ሀላባ ከተማ

ምድብ ሐ

1 ዲላ ከተማ
2 ቂርቆስ ክፍለ ከተማ
3 ስልጤ ወራቤ
4 አርባምንጭ ከተማ
5 ኢትዮጵያ መድን
6 የካ ክፍለ ከተማ
7 ደቡብ ፖሊስ
8 ነገሌ አርሲ
9 ባቱ ከተማ
10 ሺንሺቾ
11 ቡታጂራ
12 ኮልፌ ክፍለ ከተማ

የምድቦቹ ደረጃዎች ከወጣ በኋላም የመጀመሪያ ሳምንት የጨዋታ መርሐ-ግብሮች ታውቀዋል።

የመጀመሪያ ዙር ውድድሩን ባቱ ስታዲየም ላይ የሚያደርገው ምድብ ሀ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች

ሰሜን ሸዋ ደ/ብርሃን – አክሱም ከተማ
ደደቢት – ሰሎዳ አድዋ
ለገጣፎ ለገዳዲ – ገላን ከተማ
ኢትዮ ኤሌክትሪክ – መከላከያ
ፌዴራል ፖሊስ – ወሎ ኮምቦልቻ
ወልድያ ከተማ – ደሴ ከተማ

የመጀመሪያ ዙር ውድድሩን ሀዋሳ ስታዲየም ላይ የሚያደርገው ምድብ ለ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች

ጅማ አባ ቡና – ሀላባ ከተማ
ነቀምት ከተማ – አቃቂ ክ/ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ – ካፋ ቡና
ሀምበሪቾ ዱራሜ – ወላይታ ሶዶ
ሻሸመኔ ከተማ – ቤንች ማጂ ቡና
ጋሞ ጨንቻ – ኤ.ኮ.ስ.ኮ

የመጀመሪያ ዙር ውድድሩን ጅማ ስታዲየም ላይ የሚያደርገው ምድብ ሐ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች

ዲላ ከተማ – ኮልፌ ክ/ከተማ
ቂርቆስ ክ/ከተማ – ቡታጅራ ከተማ
ስልጤ ወራቤ – ሺንሺቾ ከተማ
አርባምንጭ ከተማ – ባቱ ከተማ
ኢትዮጵያ መድን – አርሲ ነጌሌ
የካ ክ/ከተማ – ደቡብ ፖሊስ

©ሶከር ኢትዮጵያ