​የቅዱስ ጊዮርጊስ ጊዜያዊ አሰልጣኝ…

የኤርነስት ሚድንዶርፕን ስንብት ተከትሎ የፈረሰኞቹ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው ማሂር ዴቪድስ ማነው?

በቅርቡ ረጅም ልምድ ያካበቱትን ጀርመናዊውን የቀድሞው ካይዘር ቺፍስ አሰልጣኝ ኤርነስት ሚድንዶርፕን በሦስት ዓመት ውል ካስፈረመ በኃላ በይድነቃቸው ተሰማ የማሰልጠኛ ማዕከል ልምምዱን አጠናክሮ ሲሰራ ሰንብቶ አሰልጣኙ በሀገሪቱ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት የመልቀቅ ጥያቄ በማቅረባቸው ከክለቡ ጋር መለያየታቸው በዛሬው ዕለት ይፋ መደረጉ ይታወቃል። 

ጀርመናዊው አሰልጣኝ በቅድመ ውድድር ዝግጅት ወቅት በሥራቸው ከነበሩ ረዳቶች መካከል የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ያለው ማሂር ዴቪድስ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በደቡብ አፍሪካ እግርኳስ ተስፋ ሰጪ አጀማመር እያደረገ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ አሰልጣኝ ሳንቶስ ኤፍ ሲ በተባለው የደቡብ አፍሪካ ክለብ ውስጥ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ጅማሮን ካደረገ በኃላ በተመሳሳይ ማሪትዝበርግ ዩናይትድ (የሚደንዶርፕ ረዳት) እና ኤፍ ሲ ስታርስ በተባሉ ቡድኖች ውስጥ በተመሳሳይ ረዳት ሆኖ ሰርቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አያክስ ሲቲ ዩዝ ፣ ኬፕ ኡመያ የተባሉ ቡድኖችም ውስጥ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ካገለገለ በኃላ ከሳምንታት በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ረዳት ለመሆን ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል። አሁን ደግሞ የዋና አሰልጣኙን ስንብት ተከትሎ ክለቡን በጊዜያዊነት እንደሚመራ ተገልጿል።

©ሶከር ኢትዮጵያ