አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ስለ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ዝግጅታቸው ይናገራሉ

የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ለኮንፌፌሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ቡድናቸው ስላደረገው ዝግጅት፣ የቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ወደ ቱኒዚያ ከማምራታቸው በፊት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል።

ስለ ዝግጅት 

ጎንደር ላይ ነው ዝግጅት የጀመርነው። ከጎንደር የተሳካ የዝግጅት ጊዜ በኋላ ወደ አዲስ አበባ አቅንተን ብሔራዊ ቡድን ላይ የነበሩ ልጆችን በመቀላቀል ዝግጅታችንን ቀጥለናል። እንደ ቡድን ያለንበት ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት የወዳጅነት ጨዋታ ማግኘት ነበረብን። ከወልቂጤ ከነማ ጋር ተነጋግረን መጫወት ችለናል። በአጠቃላይ ነባሮቹ፣ ብሔራዊ ቡድን ላይ የነበሩት እና አዲስ ያመጣናቸውን አንድ ላይ ተቀላቅለው እንደ ቡድን የሆነ ነገር ለማየት ችለናል። እንግዲህ በዚህ ደረጃ ነው ለውድድሩ የተዘጋጀነው።

ጉዳት እና ተያያዥ መረጃ

በቡድናችን ውስጥ ምንም አይነት የጉዳት ዜና የለም። በተጨማሪም ሁሉም ከኮቪድ 19 ነፃ ናቸው። ለጨዋታው ሙሉ ስብስቡ ዝግጁ ነው ።

አላማ

ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍን አስበን ነው እየተዘጋጀን ያለነው። ከሜዳ ውጪ በምናደርገው ጨዋታ ለማሸነፍ የሚያስችለን ነገር ሁሉ ነው አቅደን የተዘጋጀነው። ያ ካልሆነ ደግሞ አቻ ወጥተን ወይም ለመልሱ ጨዋታ ልንገለብጠው የምንችለው ውጤት ይዘን ለመምጣት እየሰራን ነው ያለነው። ፍላጎታችንም እቅዳችንም በዛ መልክ ነው።

የመልስ ጨዋታ…

የመልሱ ጨዋታ አዲስ አበባ የሚደረግ ይመስለኛል። ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።

© ሶከር ኢትዮጵያ