ከፍተኛ ሊግ | ሻሸመኔ ከተማ አሰልጣኝ ሾሟል

ሻሸመኔ ከተማ የቀድሞው አሰልጣኙ አንዱዓለም ረድኤትን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ተወዳዳሪ የሆነው የምድብ ለ ክለብ ሻሸመኔ ከተማ ከአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ጋር ይቀጥላል ተብሎ ቢጠበቅም አሰልጣኙ ለአዳማ ከተማ በረዳት አሰልጣኝነት ጥሪ የቀረበላቸው በመሆኑ ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር እንቅስቃሴ ካደረገ በኋላ የተሰረዘውን የውድድር ዓመት የክለቡ ረዳት አሰልጣኝ የነበረው አንዱዓለም ረድኤትን ምርጫው አድርጓል፡፡

በሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ከ1980ቹ መጨረሻ ጀምሮ ወደ ማሰልጠኑ ከገቡ አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆነው አንዱዓለም በአሰልጣኝነት ዘመኑ ከ17 ዓመት በታች ታዳጊዎችን በከተማዋ ሰብስቦ በማሰልጠን ጅማሮን ያደረገ ሲሆን ሻሸመኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተባለን ቡድንም አሰልጥኖ አሳልፏል፡፡ አሰልጣኙ ሻሸመኔ ከተማን በረዳት እና ዋና አሰልጣኝነት ከዚህ ቀደም ማሰልጠን የቻለ ሲሆን የተሰረዘውን የውድድር ዓመት ክለቡን በረዳትነት ካገለገለ በኃላ የዋና አሰልጣኝነት ቦታ ዘንድሮ ተሰጥቶታል፡፡

አዲሱ አሰልጣኝ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከነገ ጀምሮ ለ2013 የውድድር ዓመት አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በማስፈረም ወደ ዝግጅት ይገባሉ፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ