ሴካፋ U-20 | አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ስለዛሬው ድል…

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ቡድናቸው በሴካፋ ዋንጫ ሁለተኛ ጨዋታው ድል ካደረገ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

በምድብ ሦስት ተደልድሎ በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ በኬንያ 3ለ0 የተረታው ቡድኑ በዛሬው ዕለት በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ሱዳንን ገጥሞ ሁለት ለምንም ከመመራት ተነስቶ የኢትዮጵያ ቡናው የተስፋ ቡድን ተጫዋች በየነ ባንጃ በጨዋታ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በየነ በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠሯቸው ጎሎች 3ለ2 አሸንፈዋል። ከዛሬው ድል በኋላ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከእረፍት በኃላ ምን አይነት ለውጦችን ተጠቅመው ከመመራት ተነስተው እንዳሸነፉ እና ስለ ድሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተውናል፡፡

“ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ሁለት ለባዶ እየመሩን ሱዳኖች ማፈግፈግ ጀመሩ። እኛም የነሱን መከላከል ተመልክተን ከእረፍት በኋላ የአጥቂ ቁጥራችንን አብዝተን ለመግባት በማሰብ በመጀመሪያ ከነበረው 4-3-3 ፎርሜሽን አማካይ ቀንሰን አጥቂ በማብዛት ወደ 4-2-4 ለውጠን ገባን። ይሄን ስናደርግ ደግሞ በኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተከላካዮቻቸው እንደሚረበሹ አወቅን ነው። ከአራቱ አጥቂዎች አንዱ ፍፁም ቅጣት ምት አስገኘ፣ አንዱ ሁለት ጎል አገባ፣ አንዱ ደግሞ የጎል ዕድል ፈጠረ። በዚህም ምክንያት ያሰብነው ተሳክቶልናል። ከታክቲክ ለውጡ በተጨማሪ ከሁሉም በላይ የፈጣሪ እርዳታ ታክሎበት በእረፍት ሰዓት ተጫዋቾቹ አዕምሯቸውን እንዲያስተካክሉ ነግረናቸው ነው የገባነው። በአጠቃላይ ባደረግነው እንቅስቃሴ እና ባሳካነው ድል ደስ ብሎኛል። ”

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ