አዳማ ከተማ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በበርካታ አዳዲስ ተጫዋቾች እየተዋቀረ የሚገኘው አዳማ ከተማ ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡

በአሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል እና ረዳቶቹ የሚመራው አዳማ ከተማ የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር ቅድመ ስምምነት የፈፀመ ቢሆንም ከዝውውሩ መከፈት ወዲህ ግን ወሳኝ ያላቸውን ተጫዋቾች በማስፈረም እንዲሁም ደግሞ ስምምነት ፈፅመው የነበሩትን በሙከራ ሲመለከት ቆይቶ ወደ ልምምድ ከገባ ሳምንታት አልፈውታል፡፡ የነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት ያራዘመው ክለቡ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾቹን ታፈሰ ሰርካን ከመቐለ አክሊሉ ተፈራን በይፋ ከሀዋሳ ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን የቡድኑ አካል አድርጓል፡፡

ተከላካዩ ወንድይፍራው ጌታሁን (ቦልተና) አዳማ ከተማን የተቀላቀለ ተጫዋች ሆኗል፡፡ ይህ የቀድሞው የኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ቡና የኃላ መስመር ተጫዋች የተሰረዘውን የ2012 የውድድር ዓመት በሰበታ ከተማ ካሳለፈ በኃላ ለዘንድሮ ማረፊያውን አዳማ አድርጓል፡፡

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሔር አዳማ ከተማን በይፋ ተቀላቅሏል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን የክለቡ ህይወትን የጀመረው እና ባለፈው ዓመት ወደ ዋናው ቡድን የማደግ ዕድል የነበረው ወጣቱ ተጫዋች በቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰላፊነት ዕድልን ባለማግኘቱ ለአዳማ ከተማ ፊርማውን አኑሯል፡፡

ሦስተኛው ቡድኑን የተቀላቀለው አካሉ አበራ ነው፡፡ የግራ መስመር ተከላካዩ ከዚህ ቀደም በሀላባ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ እና እንዲሁም ያለፈውን ዓመት ደግሞ በሻሸመኔ ከተማ ተጫውቶ አሳልፏል።

አዳማ ከተማ በስብስቡ ውስጥ በርካታ ወጣት ተጫዋቾች በአብዛኛው የያዘ ሲሆን ከሰሞኑ በውሰት የሲዳማ ቡናውን አጥቂ ፀጋዬ ባልቻን ለማምጣት በሂደት ላይ መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ