​በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ፋሲል ከነማ ሸንፈት አስተናግዷል

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ የቱኒዚያው ሞናስቲርን ከሜዳው ውጪ የገጠመው ፋሲል ከነማ 2-0 ተሸንፏል።

ዐፄዎቹ ከስምንት ወራት በኋላ ባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታ አዲስ ፈራሚዎቹ ሳሙኤል ዮሐንስ፣ ይሁን እንደሻው እና በረከት ደስታ በመጀመርያ አሰላለፍ ተካተው ለቡድኑ የመጀመርያ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

ሦስት ሰዓት ሲል የተጀመረው ጨዋታ ጎል የተስተናገደበት ገና በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ነበር። በ3ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን የቅጣት ምት ራሱን ከነፃ አድርጎ የተቀበለው አሊ ኦማሪ ወደ ጎልነት ቀይሮት ገና በጊዜ ሞናስቲርን መሪ አድርጓል። ከዚህች ጎል በኋላ ዐፄዎቹ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል አምርተው አቻ ለመሆን በእጅጉ ተቃርበው ነበር። ሆኖም ሽመክት ጉግሳ ያሻገረለትን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። 

ከጎሉ በኋላ የተመጠጣነ እንቅስቃሴ በቴየበት የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ወደ ጎል የመድረስ ሙከራዎች የነበሩ ሲሆን ጥሩ የጎል እድሎችን በመፍጠሩ ከገድ ግን ባለሜዳዎቹ የተሻሉ ነበሩ። በ11ኛው ደቂቃ ሚሞኒ ፉቼኒ በሞናስቲር በኩል፤ በ20ኛው ደቂቃ ሽመክት የቀነሰለትን በረከት መትቶ ቋሚውን ጨርፎ የወጣበት ደግሞ በፋሲል በኩል የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።

ከእረፍት መልስ ተሻሽለው በመግባት ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት ሞናስቲሮች በአጋማሹ በርካታ የጎል ዕድሎች መፍጠር ችለዋል። በ56ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ በተከላካዮች ተገጭቶ ሲመለስ ያገኘው ፋህሚ ቤን ረመዳን በጭንቅላት ገጭቶ ወደ ጎልነት በመቀየር የባለሜዳዎቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። 

ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ተደጋጋሚ እድሎችን የፈጠሩት ሞናስቲሮች በተለይ ከ 70ኛው ደቂቃ ጀምሮ በተከታታይ በአሊ አሞሪ፣ ፋህሚ ቤን ረመዳን፣ አልጃላሲ አማካኝነት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል። 

ከእረፍት መልስ እምብዛም ወደ ተጋጣሚ ጎል ክልል መዝለቅ ያልቻሉት ፋሲሎች በመጨረሻ ለመልሱ ጨዋታ ተስፋ የሚሰጣቸውን ጎል ለማግኘት በእጅጉ ተቃርበው ነበር። በ88ኛው ደቂቃ ላይ ሙጂብ ቃሲም ወደ ጎል ለመምታት ያደረገውን ሙከራ ተከላካይ ተደርቦ ሲመልስበት ይሁን እንደሻው ከግቡ በቅርብ ርቀት በጥሩ አቋቋም ላይ ሆኖ ቢያገኘውም የመታውን ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይታይበት በሞናስቲር 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ በቀጣይ ሳምንት የሚደረግ ሲሆን በድምር ውጤት አሸናፊው ቡድን በአንደኛ ዙር የሊቢያው አህሊ ትሪፖሊን የሚገጥም ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ