​ፋሲል ከነማ የመልስ ጨዋታውን የሚያደርግበት ሜዳ ታውቋል

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመርያውን ጨዋታ ከሜዳው ውጭ የተጫወተው ፋሲል ከነማ የመልሱን ጨዋታ የሚያደርግበት ሜዳ ታውቋል። 

ዐጼዎቹ ከቱኒዚያው ዩኤስ ሞናስቲር ጋር ባሳለፍነው ሳምንት ጨዋታቸውን አድርገው ሁለት ለዜሮ በሆነ ውጤት ተሸንፎ መመለሱ ይታወሳል። የመልሱን ጨዋታ በሜዳው በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚያደርጉ ቢታሰብም አሁን ካለው ሀገራዊ ሁኔታ አንፃር የሚጫወቱበት ሜዳ እንደ ብሔራዊ ቡድኑ ሁሉ አዲስ አበባ ስታዲየም ሊሆን እንደሚችል ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወቃል።

አሁን ባገኘነው መረጃ መሠረት ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚደረግ ማረጋገጥ ችለናል። ለዚህም ካፍ ውድድሩን የሚመሩትን ዳኞች፣ ኮሚሽነሮች እና የኮቪድ ፕሮቶኮል ተወካዮችን በሙሉ ጨዋታው አዲስ አበባ እንደሚደረግ በላከላቸው ደብዳቤ አሳውቋቸዋል። ይህን ተከትሎ ጨዋታው አዲስ አበባ እንደሆነ ሲታወቅ እሁድ ህዳር 27 ቀን 2013 በ10:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲደረግ መርሐግብር ወጥቷል።

ፋሲል ከነማ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ዩ ኤስ ሞናስቲርን ከሁለት ጎል በላይ በማስቆጠር የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብቷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ