በታንዛንያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ አመርቂ ያልሆነ ውጤት አስመዝግቦ የተመለሰውን ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ላይ ስለነበረው ቆይታ አሰልጣኙ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ወሎ ሠፈር በሚገኘው የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት በዘጠኝ ሰዓት ላይ ሠላሳ ደቂቃ በቆየው አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በመግቢያ ንግግራቸው ይህኖ ብለዋል። ” ወደ ታንዛንያ ልንጓዝ ሰባ ሁለት ሰዓት ሲቀረው ሁለት ተጫዋቾች በኮሮና ፖዝቲቭ ሆነው በመገኘታቸው አንድ ግብጠባቂ እና አማካይ ይዘን ወደ ስፍራው ልንጓዝ አልቻልንም። በዚህም ምክንያት አስራ ስምንት ተጫዋቾችን ይዘን መሄድ ችለናል። በመጀመርያው የኬንያ ጨዋታ ሦስት ለዜሮ በሆነ ውጤት ሽንፈት አስተናግደናል። በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀስን ቢሆንም ተሸንፈናል። በሁለተኛው የሱዳን ጨዋታ የመጀመርያውን አጋማሽ ሁለት ጎል አስተናግደን የነበረ ቢሆንም ከእረፍት መልስ በአስደናቂ ሁኔታ ሦስት ጎሎች አስቆጥረን ማሸነፍ ችለናል። እንደ አጠቃላይ ታንዛኒያ በቆየንባቸው የውድድር ጊዜያት ያቀድነውን ማሳካት ባንችልም ተስፋ ሰጪ ወጣት ብሔራዊ ቡድን እንዳለን ማሳየት ችለናል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የሱዳኑ ጨዋታ ነው።”
በመቀጠል በዕለቱ በቦታው ከተገኙ ጋዜጠኞች ቡድኑ በታንዛንያ ቆይታው ድክመቱ ምን ነበር? ያላሳካው እቅድ ምንድነው? በቀጣይ ከድክመቶች በመነሳት የተሻለ ቡድን ለመገንባት ምን ታቅዷል? እና ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄዎች ቀርቦላቸው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በዚህ ዙርያ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
” በውድድሩ ላይ የቡድኑ ድክመት የነበረው ከመሄዳችን በፊት እንደተናገርነው የአየር ላይ ኳስ የመከላከል አቅማችን እንደ ሀገር ችግር አለብን። ይህ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደማይጠፋ እናውቃለን። ነገር ግን መቀነስ አለብን ብለን ሠርተን ነበር የሄድነው። ሆኖም ውድድሩ ውስጥ ስንገባ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ነው የገባነው። ከገቡብን አምስት ጎሎች ሦስቱ የአየር ላይ ኳሶች ናቸው። ሰራነው፣ አሻሻልነው ያልነው ችግር ነው እዛ ሄደን ያጋጠመን። በተመሳሳይ የሀገራችን ክለብ የሆነው ፋሲል ከነማ ቱኒዚያ ሄዶ በተመሳሳይ መንገድ ነው ጎል ገብቶበት የተሸነፈው። ስለዚህ እንደ ሀገር ይህ ችግር አለብን በማለት መሥራት ይጠበቅብናል። ያዋጣናል ብለን ባሰብነው ለምሳሌ ሁለቱ የመሐል ተከላካዮች ከሜትር ከሰማንያ በላይ ናቸው። ስለዚህ ተክለ ሰውነት ብቻውን ይሄን ችግር ሊቀርፈው አልቻለም። ሌላ ሥራ ይፈልጋል ማለት ነው። ለዚህም ጠንክረን መስራት እንዳለብን ተምረናል።
“ያላሳካነው እቅድ… ወደ ስፍራው ስንጓዝ የአፍሪካ ዋንጫ መግባት አለብን ብለን ነበር። ይህን ያላሳካንበት ምክንያት ተጋጣሚዎቻችን ባህላቸው አድርገው በወሰዱት ቅድም ባነሳሁት ነገር ውጤታማ ሆነውበታል። እኛ ደግሞ ያንን ቀርፈን መውጣት አልቻልንም። ስለዚህ ተሸናፊ ሆነናል። የነበሩብንን ድክመቶች ጨርሶ አለማጥፋታችን እቅዳችንን እንዳናሳካ አድርጎናል።
“ቀጣይ እቅዴ የአንድ ዓመት ኮንትራት አለኝ ከፌዴሬሽኑ ጋር ተነጋግረናል። የተለያዩ ግኑኝነቶች እያደረግን ነው። የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ለማድረግ ቴክኒካል ዳይሬክተሩም እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ስለዚህ የወዳጅነት ጨዋታዎች እንዲዘጋጁ ይደረግና ልጆቹ ተሰባስበው የሚሰሩበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስለዚህ ብሔራዊ ቡድኑ የማይበተንበትንና ለዋናውን ብሔራዊ ቡድን የሚተካ ተስፋ ሰጪ ነገር የተመለከትንበት እንደሆነ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረናል።
” የዕድሜ ጉዳይን በተመለከተ እንደሚታወቀው ከሰባት ወር በላይ እግርኳሳችን በኮሮና ምክንያት ተቋርጧል። እንቅስቃሴዎች የሉም። እንቅስቃሴዎች ሲቆሙ ደግሞ የትኛውም ሊግ ቆሟል ማለት ነው። የ20 ዓመት በታች ተጫዋቾች እነማን እንደሆኑ አናውቃቸውም ማለት ነው። ስለዚህ ያለው አማራጭ እዚህ ሊግ ላይ ሰዎችን የማናገኝ ከሆነ የፕሪምየር ሊግ ቡድኖች በወደ ልምምድ ስለገቡ እየሰሩ በመሆናቸው ለዚህ ውድድር በእድሜ ይመጥናሉ ያልነውን እና ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ውስጥ የተለየ አቅም ያላቸውን እንደ በየነ ባንጃ፣ ሙሴ ከበላ፣ አብርሃም ጌታቸው እና አማኑኤል ተርፋን መርጠናል። እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ ትክክለኛ የዕድሜ መለኪያ የለም። ኤምአርአይ ስንጠቀም ነው የነበረው። በዚህ ውድድር ላይ ደግሞ ፓስፖርት ስንጠቀም ነው የቆየነው። ስለዚህ በፓስፖርት ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሚል ስለሆነ እና ሌላ መለኪያ ስለሌለን እነዚህን ልጆች ብሔራዊ ቡድን ላይ አካተናል። ውድድሩ ላይም ተመሳሳይ ነገር ነው የገጠመን። ሱዳን እና ኬንያ ይሄንን ነው ያደረጉት። በመሆኑም ውድድሩ በሚፈቅድልን መሠረት ምርጫ አድርገናል። ከግምት ውጭ ሌላ የምናደርገው ነገር የለም”።
© ሶከር ኢትዮጵያ