ስለ በቀለ እልሁ ሊያውቋቸው የሚገቡ ዕውነታዎች

ሜዳ ውስጥ ለለበሰው መለያ ሟች ነው። ሁሉን ሳይሳሳ አውጥቶ በመስጠት፣ በአልሸነፍ ባይነቱ፣ በታጋይነቱ እና በጠንካራ ሠራተኝነቱ ይታወቃል። ጥቂት በማይባሉ ክለቦች በነበረው የእግርኳስ ሕይወቱ በአመዛኙ በቋሚነት የተጫወተው ያልተዘመረለት የዘጠናዎቹ ኮከብ በቀለ እልሁ (እልሁ) ማነው ? 

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ በቀደመውም ሆነ በአሁኑ ዘመን በርካታ ተጫዋቾችን እያፈራች መሆኗ ብዙም በማይነገርላት ቢሸፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ ነው የዛሬው ባለታሪካችን የተወለደው። በጊዜያቸው ከክለብ እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ መጫወት የቻሉትን ድንቅ ተጫዋቾች መሰለ አካለወልድ ፣ ቅጣው ሙሉ ፣ ዓለምእሸት የመሳሰሉትን እየተመለከተ አድጓል። ይልቁንም ከቤቱ አቅርቢያ በሚገኘው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ግቢ ውስጥ በመጫወት አሳልፏል። በሰፈር ውስጥ በቀበሌ ቡድን መጫወት የጀመረው ይህ የቀድሞ ድንቅ አማካይ እና ተከላካይ በተወደደበት ከተመ ለአንድም ክለብ ሳይጫወት እንዲሁም በነበረው አቅም በቀጥታ ወደ ዋና ቡድን በመቀላቀል የእግርኳስ ህይወቱን “ሀ” ብሎ ጀምሯል።

በአልሸነፍ ባይነቱ፣ በሸርተቴዎቹ፣ ጉልበትን ተጠቅሞ በመከላከሉ እና ወደ ፊት በመሄደ ጎል በማስቆጠር አቅሙ ብዙዎች የሚያውቁት በቀለ እልሁ በ1987 የመጀመርያው ክለብ ይሆን ዘንድ በሁለት መቶ ብር ደሞዝ በአሰልጣኝ ጌታሁን ገብረ ጊዮርጊስ የሚመራው አየር መንገድን ተቀላቅሏል። ገና ታዳጊ የነበረ በመሆኑ ‘ይህን ልጅ ዋና ቡድን ማጫወት ተገቢ አይደለም’ በማለት ብዙዎች ቢቃወሙትም ያለውን ፈተና በማለፍ ለአየር መንገድ ሁለት ዓመታትን ከተጫወተ በኃላ ጉዳት በማስተናገዱ ከቡድኑ ተቀንሶ ወደ ተወለደበት ሀገር ቢሾፍቱ በመመለስ እየኖረ ሳለ የሙገር አሰልጣኝ ታምሩ በቀለ ‘ለሙገር ተጫወት’ ብሎ ሲጠራው አጋጣሚ ሆኖ ከማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታ ጋር ሜክሲኮ አካባቢ በአካል ይነገናኛል። ጋሽ ሐጎስም ‘ምን ሆነህ ነው የጠፋህው ? በጣም እያፈላለኩ ነበር። መልዕክትም ልኬብህ ነበር መልዕክቱ አልደረሰህም ፤ የጤናህ ሁኔታ አሁን እንዴት ነው ? ተሻለህ አሁን ? ጤንነትህ ጥሩ ከሆነ የትም አትሄድም እዚሁ እኔ ጋር ትጫወታለህ’ በማለት ከ1989-1991 ድረስ ለሦስት ዓመት ለመብራት ኃይል በመጫወት የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን እና ሊጉ በአዲስ የውድድር አቀራረብ መካሄድ በጀመረበት ዓመት የመጀመርያውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ በማንሳት ስኬታማ ቆይታን አድርጓል። ሆኖም ጋሽ ሐጎስ በህመም ምክንያት በማይገኙባቸው ጊዜያት በወቅቱ በነበረው አስቸጋሪ ነገሮች ከስምምነት ሊደርስ ባለመቻሉ በመጨረሻም በመብራት ኃይል ለመቆየት የነበረው ፍላጎት ሳይሳካ ወደ ሌላ ክለብ ለማምራት ተገዶ ነበር። 

በአንድ ክለብ ረጅም ዓመት በመጫወት ያሳለፈበት እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ለመመረጥ ወደቻለበት እንዲሁም ምርጥ አቋሙን ወዳሳየበት ኒያላ በማምራት ቡድኑ ከአዲስ አበባ ዲቪዚዮን እስከ ፕሪምየር ሊግ ድረስ ከፍ ብሎ እንዲጫወት በማስቻል የበቀለ እልሁ የአምስት ዓመታት ቆይታ ከፍተኛ አስተዋፆኦ ነበረው።

በኒያላ አብሮት የተጫወተው የቀድሞው ድንቅ አማካይ ጌታቸው ካሣ (ቡቡ) ስለ በቀለ እልሁ ሲናገር “በቀለ በጣም ጎበዝ የሆነ መሸነፍ የማይወድ ተጫዋች ነው። በቦታው ሁሉን ነገር አሟልቶ የያዘ አንድ ቡድን በእርሱ ቦታ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ በሚገባ የያዘ ተጫዋች ነው። በዛ ላይ በሜዳም ከሜዳም ውጪ በጣም ሥነ ስርዓት ያለው ሰው ነው። እለኸኛ እና ጠንካራ ተጫዋች ነበር። እርሱ ሜዳ ውስጥ ካለ ብዙ ስጋት የለብህም በኮፊደንስ እንድትጫወት የሚያደርግህ ተጫዋች ነበር።” ይላል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ በአርጀንቲና ዓለም ወጣቶች ዋንጫ ተሳትፎ ባደረገችበት ውድድር በሦስቱም የምድብ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ የቻለው በቀለ ጥንካሬውን ከማሳየቱ ባሻገር በተጨማሪም በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ ከሀገር ውጪ ለመጀመርያ ጊዜ ዋንጫ ይዛ ስትመለስ በቡድኑ ስብስብ ውስጥ የነበረ ተጫዋች ነው።
ከኒያላ የአምስት ዓመታት ቆይታ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የመግባት ዕድል ቢያገኝም እንደሱ አገላለፅ ‘በአንድ ሰው ተንኮል’ ምክንያት ዕድሉ በመጨናገፉ የሚቆጨው በቀለ በመቀጠል ወደ ንግድ ባንክ አምርቶ ቢጫወትም በአንዳንድ ነገሮች ባለመስማማት በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሚሰለጥነው አዳማ ከተማ ተጫውቷል። ድሬዳዋ ከተማ፣ በድጋሚ ንግድ ባንክ በኃላም ለሦስት ዓመታት በሻሸመኔ ከተማ ቆይታ አድርጎ ባጋጠመው የዲስክ መሸራተት ህመም ምክንያት ብዙ መጫወት የሚችልበት አቅሙ እያለው በአሳዛኝ ሁኔታ በ2003 ጫማውን ለመስቀል ተገደደ።

የወቅቱ የሰበታ ከተማ ምክትል አሰልጣኝ እና የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች ይታገሱ እንዳለ ስለ በቀለ ምስክርነት ሲሰጥ “በቀለ በአዳማ አብሬው መጫወት ችያለሁ። የእግርኳስ ችሎታው እንዳለ ሆኖ እኔ ከእርሱ አስቀረሁት የምለው እና በጣም የሚገርመኝ በሜዳም ከሜዳ ውጪ ያለው ባህሪው ነው። ሌላው በቦታው ለአንድ ቡድን መስጠት የሚገባውን የሚሰጥ መሸነፍ የማይወድ ጠንካራ ተጫዋች ነበር።” በማለት ይገልፀዋል።
ከእግርኳስ ተጫዋችነቱ ቢገለል በቀለ ወደ አሰልጣኝነቱ በመግባት የተለያዩ ኮርሶችን እስከ ቢ ላይሰንስ ድረስ በመውሰድ ቡሌ ሆራ እና ዶዶላ ክለብን ቢያሰለጥንም እርሱ ከመጣንበት መንገድ አንፃር በኢትዮጵያ እግርኳስ ግልፅ የሆነ መንገድ ባለመኖሩ የማሰልጠን አቅም እያለው በአሁኑ ወቅት ራሱን ደብቆ በቤቱ ተቀምጦ እየኖረ ይገኛል። በዘጠናዎቹ ከተፈጠሩ ምርጥ ተጫዋች ከሆነው በቀለ እልሁ ጋር ሶከር ኢትዮጵያ ያደረገችው ቆይታ ይህን ይመስል ነበር።

“በተጫወትኩበት የእግርኳስ ዘመኔ ያላገኘሁት ዋንጫ የለም፤ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። በመብራት ኃይል፣ በኒያላ በሌሎቹም ክለቦች ጥሩ ቆይታ አድርጌያለሁ። ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመርያውን የዓለም ወጣቶች ዋንጫ በተሳተፈችበት ቡድን ውስጥ ሦስቱንም ጨዋታ በቋሚነት መጫወት ችያለሁ። ከሀገር ውጪ ለመጀመርያ ጊዜ ዋንጫ ይዞ በመጣው ዋናው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ነበርኩ። በአጠቃላይ ወደ አስራ ስባት ዓመት ያህል በጥንካሬ ያለኝን ነገር ሁሉ አውጥቼ በመስጠት መጫወት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ።
” ኒያላ የወረድበት መንገድ በጣም የምቆጭበት ነው። ከዚህ ውጪ ከኢትዮጵያ ወጥቶ የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። በእኛ ጊዜ ውጪ ወጥቶ የመጫወት ነገር ከባድ ቢሆንም በአርጀንቲና የነበረውን የተስፋ ጭላጭል አለመጠቀሜ ይቆጨኛል። ምክንያቱም ወጥቶ የመጫወት አቅሙ ነበረኝ። ጊዜው አስቸጋሪ በመሆኑ እና እከክልኝ ልከክልህ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ በመጠቃቀም የሚወጣ ስለሆነ ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህ ሁሌም እቆጫለሁ።

“የአርጀንቲናው የዓለም ዋንጫ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍንበት እና በቡድኑ ውስጥ መከባበር ጥሩ ፍቅር የነበረበት ጊዜ ነው። ሁላችንም አንድ ነበርን ፤ መናናቅ የሚባል ነገር አልነበርም ፤ መከባበር ነበር። እርስ በእርስም ብቻችን ያለ አሰልጣኝ ሁሉ እናወራ ነበር። ያው ልምድ የምትባል ነገር ዋጋ አስከፍላናለች እንጂ የኢትዮጵያ እግርኳስ ምን እንደሚመስል ለዓለም ህዝብ አስተዋውቀናል።
“መብራት ኃይል የነበረኝ ቆይታ በጣም አሪፍ ነበር። እንዳውም ብዙዎች የሚያስቡት ከመብራት ኃይል ሲ እና ቢ ቡድን እንደተገኘሁ ነው። ልጅ ስለነበርኩኝ ከታች ያደግኩ አድርገው ያስባሉ አየር መንገድ ከዛ በፊት መጫወቴን አያቁም። መብራት ኃይል ብዙ ዓመታት መጫወት እፈልግ ነበር። ብዙ ነገር እየተማሩኩ ብዙ ለውጥም እያመጣው በጥሩ አቋም እያገለገልኩ ነበር። ሆኖም አንዳንድ ሰዎች የሀጎስ ዘመድ ነው ይሉኛል። ቅፅል ስምም ሁሉ እያወጡልኝ ነበር። በየት ተገናኝተን ነው እርሱ ትግሬ እኔ ኦሮሞ ምን ተገናኝተን ነው ዘመዴ የሚሆነው እያልኩ እመልስ ነበር። በቃ እኔ ከእነርሱ ጋር ምን አጨቃጨቀኝ የትም ክለብ ሄጄ መጫወት የምችልበት አቅሙ አለኝ። እዚህ ክለብ ከዚህ በኃላ አልጫወትም ብዬ ወደ ሌላ ክለብ ላመራ ችያለው። እንጂ በመብራት ኃይል ብዙ ማሳካት የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩኝ። በክለብ ደረጃ ከኢትዮጵያ ውጭ ወጥቼ መጫወት የጀመርኩት በመብራት ኃይል ክለብ ነው። ሆኖም ሊያሰሩኝ ባለመቻላቸው የምወደውን ክለብ ሳልፈልግ ለመልቀቅ ተገድጃለው።

“በእግርኳስ ተጫዋች ዘመኔ በአንድ ክለብ ረጅም ዓመት የተጫወትኩት ኒያላ ነው። አምስት ዓመት ቆይቻለሁ። በጣም አሪፍ ጊዜ ነበር። ኤልያስ ጁሀር፣ ሙልጌታ ከበደ፣ ጌታቸው ካሣ (ቡቡ)ን የመሳሰሉ አንጋፋ ተጫዋቾች ሌሎችም ምርጥ ወጣት ተጫዋቾች የነበሩበት ስብስብ ነው። በአሰልጣኝነቱም አብርሀም መብራቱ የነበረበት ቡድን ነው። ከታችኛው ከአዲስ አበባ ዲቪዚዮን አንስተን እስከ ፕሪምየር ሊግ እንዲሳተፍ አድርገነው የነበረ ቢሆንም መጨረሻ በ1996 ሀዋሳ ላይ በአሳዛኝ ሁኔታ ሲወርድ አዝኛለው። አርጄንቲና የዓለም ዋንጫ በሄደው የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን እንዲሁም የሴካፋ ዋንጫ ከሩዋንዳ ይዞ ለመጣው ብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩት ኒያላ እየተጫወትኩ ነው። በአጠቃላይ ኒያላ የነበረኝ ቆይታ በጣም አሪፍ ነበር። እንዲያውም በኒያላ ቆይታዬ በ1996 ከሀዋሳ ጋር እነርሱ ለሻምፒዮናነት እኛ ላለመውረድ ስንጫወት ለሊብሮ ጋዜጣ በሰጠሁት ቃለ መጠይቅ “ኒያላ ከሚወርድ ሬሳዬ ከሜዳ ቢወጣ ይሻላል ብዬ ተናግሬ ነበር። ጨዋታው እየተካሄደ ሰብስቤ ሸገሬ አንድ አግብቶ ኒያላ እየመራ ህዙቡ እኔን ነበር የሚያውቀው እኔም አላፈናፍን ብዬ ወጥሬ ይዤ ነበር። ህዝቡም ‘በቀለ ዋ! ዋ!’ እያለ ይጮህ ነበር። በኃላም አንድ ቴዲ ሰበታ የሚባል አጥቂ ሀዋሳዎች ቀይረው አስገቡት። ቀጥታ ወደ እኔ እየሮጠ መጥቶ ዓይኔን በቦክስ ድርግም አድርጎ መትቶኝ እንዴት እንደወደቅኩ አላቀውም። ጨዋታው ስምንት ደቂቃ ያህል ተቋርጦ ነበር። እኔ ከተመታው በኃላ ዓይኔ ላይ አረንጓዴ ቀይ እና ቢጫ ነው የሚታየኝ። ሬሳዬ ይወጣል ብዬ በእውነት በትክክል አውጥቶት ነበር። ይህች ትዝታን መቼም አረሳውም።

“አልሸነፍ ባይነቱነን እና በተለያዩ ቦታዎች የመጫወት ጥንካሬውን ያገኘሁት… እኔ ሜዳ ውስጥ ከገባው ወደ ኋላ የምለው ነገር የለም። ኳሱ የሚፈቅደውን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ። መሸነፍ የሚባል ነገር አልፈልግም። በተለይ አጥቂ ኳስ ይዞ ሲያሽሞነሙን ማየት አይመቸኝም። በቃ ያልቅለታል ከነኳሱ ነው አፈር ከድሜ የማስግጠው። ይህ ደግሞ ከታች ከቀበሌ ጀምሮ ይዤው የመጣሁት ነው። ዮርዳኖስ ዓባይ ራሱ ‘አንተ ወንድምህ ቢመጣ ራሱ አትምርም፤ ትገላለህ’ ይለኝ ነበር። (እየሳቀ) እኔ ሜዳ ከገባው ቀልድ አላውቅም። ሰው ለመጉዳት ብዬ ሳይሆን ኳሱ እንዳያመልጠኝ ነው የምታገለው። ጎል ሊገባ አንግሉ ጋር እንኳን ከደረሰ ከአንግሉ ስር አውጥቼ ብዙ ጊዜ በአንግል ተፈንክቻለው። እና መሸነፍ በጣም አልወድም ነበር። በዚህም በተደጋጋሚም ጉዳት አስተናግጃለው። አሁንም ያው አልሸነፍ ባይነቴ በጤና ቡድን ስጫወት አብሮኝ አለ።
“ወደ አሰልጣኝነቱ የገባሁት ገላን አካባቢ የመጀመርያ ደረጃ ኮርስ እንደሚሰጥ ስሰማ እኔ አሸናፊ ግርማ፣ ጌታቸው ካሳ ሆነን ወሰድኩ። በዓመቱ አዳማ ላይ የሲ ላይሰንስ ኮርስ መጣ እርሱንም ወሰድኩ። በድጋሚ የ ቢ ላይሰንስ ወስጄ ቡሌ ሆራ የሚባል ቡድን በ2007 በምክትል ጀምሬ በኋላ ወደ ዋናው አሰልጣኝነት አድጌ ቡድኑን ከዝቅተኛ ነጥብ የተሻለ ነጥብ ይዞ እንዲጨርስ ማድረግ ችዬ ነበር። በቀጣዩ ዓመት ቡድኑን አጠናክሬ ጥሩ ውጤት እያስመዘገብን ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመግባት እየተቃረብን ‘ምንድነው አንተ ብዙ ወጪ ልታስወጣን ነው።’ በማለት ቡድኑ ከፍተኛ ሊግ እንዳይገባ ይጎትቱኝ ጀመር። በኋላ ለቅቄ ወጥቻለው። በመቀጠል የተወለድኩበት ከተማ ቢሸፍቱን ታሰለጥናለህ ተብዬ ነበር፤ በኋላ ቀርቷል። ዶዶላ የሚባል ከተማ ሄጄ ጥሩ ቡድን ሰርቼ ቡድኑን እያሰለጠንኩ ባለበት ሰዓት የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሹም በሥራዬ ጣልቃ እየገባ ቋሚ አሰላለፍ እያወጣ እከሌን አስወጣ አስገባ እያለ ሊያሰራኝ ባለመቻሉ ጥዬ መጥቻለው። በዚህ ሁኔታ በሁለቱ ክለቦች ማሰልጠን የጀመርኩት። አሁን ምንም እየሰራው አይደለም።

“የተሰማኝን በግልፅ መናገሬ በኢትዮጵያ እግርኳስ ክፉኛ የተጎዳ እንደኔ ያለ ተጫዋች የለም። እኛ ሀገር ውስጥ መርመርመጥ ነው ያለው። እኔ ፊት ለፊት ነው የምናገረው፤ መወሻሸት አላውቅም። ኳስ ስችል እጫወታለው ኳስ ካልቻልኩ አቆማለሁ። ከዚህ ውጭ ለአሰልጣኝ፣ ለክለብ አመራር ፀጉሬን እያከኩ በፍርሀት አላወራም። የማይሆን ነገር ካጋጠመኝ ፊት ለፊት ነው የማወራው። በዚህ ምክንያት እርሱ ተናጋሪ ነው እርሱ እንዲህ ነው እያሉ እኔ ብዙ ነገሮች ሳልጠቀም እያራቁኝ ኖሬያለሁ። ይህ ደግሞ አሁን ሳስበው በጣም ጎድቶኛል። አብረውኝ የተጫወቱ ጓደኞቼም በደንብ ያውቁታል።
“በቅፅል ስም ደረጃ የተለየ ስም አልወጣልኝም። ብዙዎች እልሁ ነው የሚሉኝ በአባቴ ስም ነው የሚጠሩኝ። የጨዋታ ባህሪዬ እልህኛ ስለሆንኩ በዚህ ይጠሩኛል። እንዲያውም አንዳንዶች የአባቱ ስም ጠቅሞታል እያሉ ይቀልዳሉ።

“1997 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ልገባ ጫፍ ደርሼ ነበር። የቡና ደጋፊም በጣም ወደውኝ ‘በቄ ለቡና ይሰራል ገና’ በማለት ሁሉ ሰበታ ላይ ዘምረውልኝ ነበር። ሆኖም ከኒያላ አካባቢ አንድ መሠሪ ሰው ነበር። በጣም በሚገርም መንገድ ለቡና አመራሮች ደውሎ ‘ ሰካራም የሆነ ተጫዋች ልታስፈርሙ እንዴት ታስባላችሁ?’ ብሎ ደውሎ ቡና የመግባት ህልሜን አበላሸብኝ። በሕይወቴ የሚቆጨኝ ነገር አንዱ ይሄ ነበር። ምክንያቱም በኒያላ ቆይታዬ ብሔራዊ ቡድን ተጠርቼ ያለኝን አቅም አሳይቻለው። ከዚህ በኋላ በሀገሪቱ ታላላቅ ክለቦች ቡና እና ጊዮርጊስ መጫወት የሚያስችል ስም ገንብቼ ነበር። ሆኖም በእንደዚህ ያለ ሴራ ምክንያት ሳይሳካ በመቅረቱ እቆጫለሁ። መብራት ኃይል እና ኒያላ እያለው ከቡና እና ከጊዮርጊስ ጋር ስጫወት አንድ ቀን መጥፎ ሆኜ አላውቅም። የሚገርም አቅሜን ነበር የማሳየው። ያሁሉ ደጋፊ እኔ ላይ ሲጮህብኝ ሲሰድበኝ እኔን እየደገፉኝ እያበረታቱኝ ነው የሚመስለኝ። የባሰ እየባሰብኝ የሌለኝን ችሎታ ነበር የማወጣው። በዚህ ሁኔታ ቡና ለመግባት ተቃርቤ በዛ ሰውዬ ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱ ያ ሰውዬ በህይወቴ ላይ ትልቅ ጠባሳ ነው አስቀምጦ የሄደው።
” በእግርኳስ ብዙ ገጠመኞች አሉኝ። በአንድ ወቅት ከባቡር ጋር አዲስ አበባ ስታዲየም ነገ ልንጫወት ዛሬ የቀድሞ አሰልጣኝ ዳኘው፣ ዳሽን የተለያዩ ክለቦች አሰልጥኗል አሁን አሜሪካ ነው ያለው። እና የእርሱ ሚዜ ነበርኩ። የክለቡ አመራሮች ነገ ጨዋታ እያለ እንዴት ሠርግ ትላላችሁ እያሉ ይናገሩ ነበር። ባቡር ድሬዳዋ ላይ አንድ ለዜሮ አሸንፎን ስለነበረ ጨዋታውን ማሸነፍ ይጠበቅብን ነበር። በጨዋታው ዕለት 3-1 ስናሸንፍ እኔ ሁለት ጎል አግብቼ ነበር። ታዲያ አንዱን ጎል ሳስቆጥር በህይወቴ የማረሳው ነገር ተከስተ። ኳሱ ከማዕዘን ምት ሲሻገር ከዳኛው አናት ላይ ኳሱ መጣ። እኔ ደግሞ ከዳኛው ከኃላ ነበርኩ። ብድግ ብዬ ኳሱን አየር ላይ እንዳለ ስመታው ኳሱ በቀጥታ ሄዶ አንግሉን ገጭቶ ጎል ተቆጠረ። ለካ እኔ ወደ መሬት ስወርድ ዳኛውን በጫማ ጥፊ አግኝቼው በፊቱ ተደፍቶ ኖሯል። እሱም ፊሽካው ተበትኖበት ከወደቀበት ደንግጦ ተነስቶ ፊሽካውን ፈልጎ፣ ለቃቅሞ ጎሉን ያፀደቀበት መንገድ በሕይወቴ መቼም አልረሳውም (…በጣም እየሳቀ)።

“አሁን የምገኝበት ሁኔታ… እንደሚታወቀው እኔ ወሬ ሌላም ነገር አልወድም። ድምፄን አጥፍቼ ተደብቄ ነው የምኖረው። አንዳንዴ የሚያገኙኝ ሰዎች ‘እንዴት አንተ ለሀገርህ ለፍተህ ሰርተህ ማሰልጠን መሥራት አለብህ’ ይሉህና እኔ እንደዚህ አደርግልሀለው ብሎ ስልክ ይሰጥሀል። ስትደውል ግን አያነሳም። በዚህ ምክንያት ስልችት ስላለኝ ተደብቄ ነው ያለሁት። በኢትዮጵያ እግርኳስ የሚያወራው ብር ያለው ሰው ነው። መሥራት ብፈገልግም በዚህ ምክንያት ርቄያለሁ። የተሻለ ነገር እስኪመጣ መጠበቅ ነው እንጂ ባለኝ የተጫዋችነት ልምድ እና ባገኘሁት ስልጠና በእግርኳስ ውስጥ ማሰልጠን በጣም ነው የምፈልገው።
“የቤተሰብ ሕይወቴ… እናቴ ጋር ነው ያለሁት። አንድ የዘጠኝ ዓመት ወንድ ልጅ ሻሻመኔ እየተጫወትኩ የወለድኩት አለ። ደብረዘይት ነው የምኖረው። የልጄ ስም አማኑኤል በቀለ ይባላል። በጣም ፈጣን ሩጭ ነው፤ ከየት እንዳመጣው አላውቅም ጎበዝ ተጫዋች ነው። ወደፊት ፈጣሪ ፍቃዱ ከሆነ የዚህች ሀገር እግርኳስ በእነርሱ ይለወጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለጤናዬ በግሌ የጤና ሰፖርት እየተጫወትኩ ነው።

“በመጨረሻም ለእግርኳስ ትልቁ ነገር ስፖርታዊ ሥነ-ምግባር ነው። ዲሲፕሊን ከሌለህ ኳስ አሽመንሙነህ ብትገፋ ዋጋ የለውም። እኛ ድሮ ስንጫወት የነ ኤልያስ ጁሀር፣ አንዋር ያሲን፣ የሌሎቹንም ትልልቅ ተጫዋቾች ከትሬኒንግ መልስ ማልያ አውልቀው ሲታጠቡ እኛ ከስር ተቀብለን ማልያቸውን አጥበን ነበር። እኛ ለእነርሱ ካለን ክብር እና እነርሱ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ነው ይህን የምናደርገው። ሲቆጡን እንሰማ ነበር በጣም መከባበር ነበር። አሁን ላይ ስታይ ይህ ነገር እየተበላሸ መጥቷል። በባለሙያው መካከል መከባበር የለም። ይህ መመለስ አለበት እግርኳሱ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ አንድነት ሊኖረው ይገባል። ሌላው በእኔ የእግርኳስ ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ፈጣሪ ነፍሱን በገነት ያኑረው እና ጋሽ ሀጎስ ደስታ ስለ እርሱ አውርቼ የማልጠግበው ሁሌም የማስበው የማከብረው ሰው ነው። የእርሱም ጓደኛ ማስተር አስማማው እሸቱ፣ አስፋው ደበሌ አጠቃላይ አየር ኃይሎች ለኔ ሁሉም ጥሩ ናቸው። ለእነርሱ ትልቅ ክብር እና ምስጋና አለኝ። አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ብሔራዊ ቡድን ስጫወት ስንት ነገር ያደረገልኝ ሰው ስለሆነ እርሱንም አመሰግናለው። እናተም አስታውሳችሁ አክብራችሁ ፈልጋችሁ ስላወራችሁኝ ሶከር ኢትዮጵያን አመሰግናለሁ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ