ኢትዮጵያዊያን በውጪ | ሽመልስ በቀለ ለተጨማሪ ዓመት በምስር ይቆያል

ከሰሞኑ ለእረፍት ኢትዮጵያ የነበረው ሽመልስ በቀለ በክለቡ ኮንትራቱ መጠናቀቁን ተከትሎ ውሉን አድሷል፡፡

በሀዋሳ ከተማ በመጫወት የክለብ ህይወቱን የጀመረው ይህ አማካይ በመቀጠል በቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም የዋልያዎቹ ወሳኝ ተጫዋች በመሆን ቀጥሏል፡፡ ተጫዋቹ ቅዱስ ጊዮርጊስን በ2005 ከለቀቀ በኋላ በሊቢያ፣ ሱዳን እንዲሁም ግብፅ ክለቦች በመጫወት የእግርኳስ ሕይወቱን እየገፋ ይገኛል፡፡

አማካዩ ድንቅ ጊዜያት ያሳለፈበት ፔትርጀትን ለቆ ወደ ሌላኛው የሀገሪቱ ክለብ ምስር ለልመቃሳ ካመራ በኃላ በተወሰነ መልኩ በፔትሮጀክት ያሳይ የነበረውን አቋም በወጥነት ማሳየት ባይችልም ጥቂት በማይባሉ ጨዋታዎች ላይ ግን ወሳኝነቱን አስመስክሯል፡፡ በክለቡ ውሉን ማገባደዱን ተከትሎ ተጫዋቹ ክለቡን በመልቀቅ ወደ ኤዥያ ወይንም ደቡብ አፍሪካ ክለቦች እንደሚያመራ ቢጠበቅም በምስር ለልመቃሳ እስከ ሰኔ ወር ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል።

በግብጽ ፕሪምየር ሊግ ያለፉትን ስድስት የውድድር ዓመታት ያሳለፈው የመሀል ሜዳው ጥበበኛ በምስር ውሉ ሲጠናቀቅ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ዳግም ተመልሶ ሊጫወት እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ ለተጫዋቾቹ ቅርበት ካላቸው ሰዎች ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ