​በወቅታዊ ሁኔታ የመሳተፉ ነገር አጠራጣሪ የነበረው ክለብ በፕሪምየር ሊጉ እንደሚሳተፍ ተረጋገጠ

የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ከዚህ ቀደም ባልነበሩ የተለያዩ በጎ ነገሮች ታግዞ የፊታችን ታኅሣሥ ሦስት ቀን በይፋ እንደሚጀመር የሊጉ አወዳዳሪ አካል ማሳወቁ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ አብዛኛው ክለቦች ቅድመ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ የውድድሩን መጀመር በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ይታወቃል። ሆኖም ባለው ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ምክንያት በተለይ ሦስቱ በትግራይ ክልል መቀመጫቸውን ያደረጉት መቐለ ሰባ እንደርታ፣ ወልዋሎ እና ስሑል ሽረ በውድድሩ የመሳተፋቸው ነገር እስካሁን ቁርጡ ያለየለት ቢሆንም ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ስሑል ሽረ በፕሪምየር ሊጉ እንደሚሳተፍ ለማወቅ ችለናል።

በአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀ የሚመሩት ሽረዎች ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ ልምምዳቸውን እንደሚጀምሩ ለማወቅ የቻልን ሲሆን በሊጉ የሚሳተፉበትን አዲስ ማልያ ከፖርቹጋል ሀገር በቅርቡ እንደሚመጣላቸው ሰምተናል።
ለቡድኑ አሁን ከባድ የሆነው እና አወዳዳሪው አካል ከነበረባቸው የስነ ልቦና ችግር ተላቀው እና በቂ የልምምድ ጊዜ አግኝተው ወደ ውድድሩ ለመግባት እንዲችሉ የእነርሱ ጨዋታ ለተወሰነ ጊዜ የሚራዘምበትን መንገድ ለመጠየቅ ለሊግ ካምፓኒው ደብዳቤ እንደሚያስገቡ ለማወቅ ችለናል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖር አዳዲስ መረጃዎች እንደደረሱን የምናሳውቅ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ