​ፋሲሎች ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅታቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ

በአፍሪካ መድረክ ያላቸውን ተሳትፎ ለማስቀጠል የፊታችን እሁድ ወሳኝ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ዐፄዎቹ በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምዳቸውን እየሰሩ ይገኛል።

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን እያደረጉ የሚገኙት ዐፄዎቹ የፊታችን እሁድ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን አዲስ አበባ ስታዲየም ያከናውናሉ። ባለፈው ሳምንት ወደ ሞናስቲር በማቅናት 2-0 ተረተው የተመለሱት ፋሲሎች የመልሱን ጨዋታ ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ጠንካራ ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። 

የሁለት ለዜሮ ሽንፈታቸውን ቀልብሰው ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በሚያደርጉት በዚህ ወሳኝ ጨዋታቸው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ዛሬ በ10:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም በነበረው ልምምዳቸው በተወሰነ መልኩ የተጨዋቾች አጠቃቀም ለውጥ እንደሚያደርጉ ፍንጭ የሰጠ ልምምድ ሰርተዋል። በተለይ ለሁለት ተከፍለው ሙሉ ሜዳ በተደረገው ጨዋታ ወደ ሞናስቲር በማቅናት በነበረው የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ይሁን እንደሻውን በማሳረፍ በዛብህ መለዮን ለመጠቀም ያሰቡ ይመስላል።

በቡድኑ ውስጥ እስካሁን ምንም አይነት የጉዳት ዜና አለመኖሩን እና ሁሉም የቡድኑ አባላት በሙሉ ጤንነት ልምምዳቸውን ሲያከናውኑ ተመልክተናል። 

የፋሲል ተጋጣሚ ሞናስቲር ዛሬ አመሻሽ ላይ አዲስ አበባ በመግባት ነገ በንግድ ባንክ ሜዳ 10:00 ላይ የመጀመርያ ልምምዳቸውን እንደሚሰሩ ለማወቅ ችለናል።

ፋሲል ከነማ ውጤቱን ቀልብሶ በድምር ውጤት ማሸነፍ ከቻለ በቀጣይ ጨዋታውን ከሊቢያው አህሊ ትሪፖሊ ጋር የሚያደርግ ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ