​ይህን ያውቁ ኖሯል? (፰) | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የሴካፋ ውድድር…

ዕለተ ሐሙስ በምናቀርበው ይህን ያውቁ ኖሯል አምዳችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የተመለከቱ እውነታዎችን በተከታታይ ሰባት ሳምንታት ስናቀርብ ቆይተናል። በተለይ ከአፍሪካ እና ዓለም ዋንጫ ውድድሮች ጋር ያሉትን ዕውነታዎች ያቀረብን ሲሆን ለዛሬም ከሴካፋ ውድድር ጋር ያሉ እውነታዎችን አጠናክረን ቀርበናል።

* ሁሉም ዓመታት በአውሮፓ የዘመን ቀመር የተቀመጡ ናቸው።

– የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከ1926 ጀምሮ ሲካሄድ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ውድድር አልተሳተፈችም። ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያው ውድድር ብቻ ሳይሆን እስከ 1966 ብሎም በአዲስ መልክ እና ስያሜ እስከ 1973 ድረስ ሲደረግ ተሳትፎ አላደረገም። 

– ሴካፋ አሁን ያለውን ይዘን ተላብሶ በ1973 በአዲስ መልክ መደረግ ሲጀምርም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አልተሳተፈም። ለተከታታይ አስር የውድድር ዓመታትም ተሳትፎ ሳታደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ በኬንያ አስተናጋጅነት በተደረገው የ1983 ውድድር ላይ መሳተፍ ጀምራለች።

– ብሔራዊ ቡድኑ አምስት ሀገራት ብቻ በተወዳደሩበት የመጀመሪያው ተሳትፎ በምድቡ አንድ ነጥ ብቻ በማግኘት የምድቡ ውራ ሆኖ ተሰናብቷል።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር የመጀመሪያ ጨዋታውን ያከናወነው ከታንዛኒያ አቻው ጋር ነው። ኖቮምበር 13 ቀን 1983 በተደረገው በዚህ ጨዋታ ላይ ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች 1-1 ጨዋታቸውን አገባደዋል።

– ብሔራዊ ቡድኑ በዚህ ውድድር የመጨረሻ ጨዋታውን ያከናወነው ዲሴምበር 10 2017 ላይ ነው። በዚህ ቀን ቡድኑ ከዩጋንዳ አቻው ጋር ተጫውቶ እንደ መጀመሪያው ጨዋታ 1-1 አቻ ተለያይቷል።

– ኢትዮጵያ የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን (ሴካፋ) ለአራት ጊዜያት አዘጋጅታለች። 1987፣ 2004 እና 2007 ላይ የተደረጉት ውድድሮች በሙሉ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የተደረጉ ሲሆን 2015 ላይ የተከወነው ውድድር ግን ከአዲስ አበባ ስታዲየም በተጨማሪ በባህር ዳር እና ሀዋሳ ስታዲየሞች ተከውኗል።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሀገሯ ከተዘጋጁት አራት ውድድሮች ሁለቱን (1987 እና 2004) ስታሸንፍ የ2006ቱን በሩብ ፍፃሜ ተፋላሚነት እንዲሁም የ2007ቱን በሦስተኛ ደረጃነት አጠናቃለች።

– በውድድሩ ላይ ያሉ ተሳታፊዎችን ለማብዛት በርካታ ሀገራት ሁለት ቡድኖችን (ከዋናው በተጨማሪ ሁለተኛ ቡድን) እንዲያወዳድሩ ይደረግ ነበር። ኢትዮጵያ ግን በውድድሩ ላይ ሁለት ቡድኖችን ይዛ ቀርባ አታውቅም።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 2019 ላይ በተደረገው እና በዩጋንዳ አሸናፊነት በተጠናቀቀው የመጨረሻ ውድድር ላይ አልተሳተፈም።

© ሶከር ኢትዮጵያ