የሰበታ ከተማ ክለብ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የኮንትራት ክፍያን አስመልክቶ ቀሪ ገንዘብ ይመለስልኝ በማለት ለፌዴሬሽኑ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አገኘ።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በ2012 ሰበታ ከተማን ለማሰልጠን የሁለት ዓመት የውል ኮንትራት በመፈረም ቡድኑን ለአንድ ዓመት ማሰልጠናቸው ይታወቃል። አሰልጣኝ ውበቱ የአንድ ዓመት ኮንትራት እየቀራቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲያሰለጥኑ ጥሪ የቀረበላቸው መሆኑን ተከትሎ ከሰበታ ጋር በስምምነት በመለያየት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን እያገለገሉ እንደሆነ ይታወቃል።
ሆኖም አስቀድሞ ለሁለት ዓመት የኮንትራት የፊርማ ለጊዜው የገንዘቡ መጠን ለመግለፅ ባልፈለግነው ስምምነት መሰረት አሰልጣኙ መውሰዳቸው ክለቡ አሳውቆ የሁለት ዓመት ፈርመው አንዱን ዓመት ሠርተው ቀሪ አንድ ዓመት ስላለ የቀሪ አንድ ዓመት ክፍያ ተሰልቶ ገንዘቡ ፌዴሬሽኑ በኩል ወይም በአሰልጣኙ በኩል ተመላሽ እንዲሆንላቸው ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አሳውቀው ነበር።
ጉዳዩን የተመለከተው ፌዴሬሽኑ በሰጠው ምላሽ አሰልጣኝ ውበቱ ሀገራዊ ጥሪ ቀርቦላቸው ክለቡ ይህን ተቀብሎ አሰልጣኙ ብሔራዊ ቡድን እንዲያሰለጥኑ ፍቃደኛ በመሆናቸው ፌዴሬሽኑ ከልብ አመስግኖ “በውል ተቀባይ እና ግዴታ በአንቀፅ 8 በተጠቀሰው መሠረት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድርገን የሾምናቸው ስለሆነ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ላደረጋችሁልን ትብብር እያመሰገንን በእኛ በኩል ምንም አይነት ክፍያ የማንከፍል መሆኑን እያሳወቅን ከዚህ ቀደም መሰል ልምድ የሌለ መሆኑን እናሳውቃለን” ብሏል።
ይህን ምላሽ ተከትሎ የሰበታ ክለብ ሥራ አስፈፃሚ በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ስብሰባ በማድረግ አቅጣጫ እንደሚሰጥ የሰማን ሲሆን በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ በኩል የሚኖር ምላሽ ካለ እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ