​የእሁዱ የፋሲል ከነማ ጨዋታ በቴሌቪዥን በቀጥታ ይተላለፋል

ከነገ በስትያ በፋሲል ከነማ እና ዩ ኤስ ሞናስቲር መካከል የሚደረገው የኮንፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደሚያገኝ ተጠቁሟል።

የ2011 የኢትዮጵያ ጥሎማለፍ አሸናፊው ክለብ ፋሲል ከነማ በሁለተኛው የአህጉራዊ የክለቦች ውድድር (ኮንፌዴሬሽን ካፕ) ላይ ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን እያደረገ ይገኛል። የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውንም ወደ ሞናስቲር በማቅናት ያከናወነ ሲሆን በጨዋታውም ሁለት ለምንም ተረቷል። ቡድኑ ከቱኒዚያ ከተመለሰ በኋላ የመልሱን ጨዋታ ለመከወን ዝግጅቱን እያከናወነ ይገኛል። ተጋጣሚው ዩ ኤስ ሞናስቲርም በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረገውን ጨዋታ ለመከወን ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ገብቷል።

ለፋሲል ከነማ ወሳኝ የሆነውን ይህንን ጨዋታም አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ (አዲስ ቲቪ) ጊዜያዊ ስቱዲዮውን በአዲስ አበባ ስታዲየም በማድረግ ለስፖርት ቤተሰቡ በቀጥታ እንደሚስተላልፍ ሰምተናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ