​በትግራይ ክልል መቀመጫቸውን ባደረጉ ክለቦች እጣፈንታ ዙሪያ ማብራርያ ተሰጠ

የትግራይ ክለቦች የሊጉ ተሳትፎን በተመለከተ አዲስ ውሳኔ ተላልፏል።

በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ስሑል ሽረ በሊጉ የመሳተፋቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። ክለቦቹ በሊጉ ይሳተፉ አይሳተፉ እስካሁን ያልተረጋገጠ ሲሆን ክለቦቹም በሊጉ ለመሳተፍ ምዝገባ እንዳላደረጉ ታውቋል። ይህንን ተከትሎ የሊግ ኩባንያው ክለቦቹ ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ምዝገባ ሳይደርጉ በእጣ ማውጣቱ መርሐ-ግብር ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል።

ከደቂቃዎች በፊት የኩባንያው የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑን መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ከሦስቱ ክለቦች ጋር እስካሁን ምንም ግንኙነት እንዳልተደረገ ገልፀዋል። ይህንን ተከትሎም ክለቦቹ እስከ ታኅሣሥ ሦስት ድረስ መጥተው በሊጉ እንደሚሳተፉ የማያረጋግጡ ከሆነ በሊጉ ሙሉ ለሙሉ እንደማይሳተፉ ተረጋግጧል። ምንም እንኳን ክለቦቹ በዘንድሮ ውድድር ባይሳተፉም በ2014 በሚኖረው ውድድር ላይ ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲሳተፉ እንደሚደረጉ ተነግሯል።

© ሶከር ኢትዮጵያ