ከፍተኛ ሊግ | ኢትዮጵያ መድን በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

የአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ ኢትዮጵያ መድን በርካታ ልምድ ያላቸውን ጨምሮ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን በቅርቡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን በይፋ ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ጨምሮ በድምሩ አስራ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ የሁለት ነባሮችን ውልም አድሷል፡፡ የቀድሞው የሙገር፣ ድሬዳዋ፣ ሀዋሳ፣ ዳሽን ቢራ እና ፋሲል ከነማ እንዲሁም ያለፈውን ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ያሳለፈው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ቢኒያም ሀብታሙ (ኦሼ) የቡድኑ የመጀመሪያ ፈራሚ ሲሆን በሐረር ቢራ፣ ወልዋሎ ንግድ ባንክ እና ዓምና በሀድያ ሆሳዕና ቆይታ የነበረው ተከላካዩ ቢኒያም ሲራጅ እና ፈጣኑ የቀድሞ የአየር ኃይል፣ ቡና፣ ደደቢት እና ሀዋሳ ከተማ አጥቂ ዳዊት ፍቃዱ (አቡቲ) ሌላኞቹ አንጋፋ የመድን ፈራሚዎች ናቸው፡፡

ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች በተጨማሪ ክለቡ ታምራት ዳኜ (ግብ ጠባቂ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ)፣ አብዱልቃድር ነስሩ (ተከላካይ ከአቃቂ)፣ ከበደ አሰፋ (ተከላካይ ከአቃቂ)፣ ወጋየሁ ቡርቃ (ተከላካይ ከሻሸመኔ)፣ ሲሳይ (ተከላካይ ከወሎ ኮምቦልቻ)፣ ዮናስ ባቤና (የመስመር አጥቂ ከአቃቂ)፣ ፉአድ መሐመድ (የመስመር አጥቂ ከቤንችማጂ)፣ አፍቅሮት ሰለሞን (የመስመር አጥቂ ከደደቢት)፣ ናትናኤል ወርቁ (አማካይ ከፋሲል ከነማ)፣ ጉልላት ተሾመ (አጥቂ ከአቃቂ ቃሊቲ) አስፈርሟል።

ክለቡ የሁለት ነባር ተጫዋቾችን ውልም አድሷል፡፡ የተከላካዩ ብርሀኑ ቦጋለ (ፋዲጋ) እና ኩማ ደምሴን ውል ነው ማራዘም የቻለው፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ