​የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 12ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የግማሽ ቀን ውሎ

ባልተለመደ ሁኔታ የተሳታፊው አባላት ቁጥር አነስተኛ እንደሆነ በታየው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 12ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኢሊሊ ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።

ምልዓተ ጉባዔው መሟላቱን ለማረጋገጥ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀኃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከአንድ መቶ አርባ ሁለት አባላት መካከል መቶ ሁለት አባላት መገኘታቸውን በድምፅ ቆጠራ ካረጋገጡ በኃላ ጉባዔው መካሄድ ጀምሯል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ጉባዔተኛውን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኃላ “በ2012 ዘመን በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሺኝ ባሰብነው እና ባቀድነው መልኩ ሙሉ ለሙሉ ማሳካት እንዳንችል አሉታዊ ተፅእኖ አሳድርቦብናል። ይሄም ቢሆን በርከት ያሉ ሥራዎችን ማከናወን ችለናል። ለአብነት ያህል የካፍ የልህቀት ማዕከል አስፈላጊውን የማስተካከያ ሥራዎችን በማስተካከል ማዕከሉ ወደ ሥራ እንዲገባ አድርገናል። ዓለም አቀፍ ግኑኝነታችንን ጠንካራ እንዲሆን በርከት ያሉ ሥራዎች ተሰርተዋል። ገቢን ለማሳደግ ከፊፋ ከካፍ የሚሰጠው ድጎማ እንዳለ ሆኖ ከስፖንሰር፣ ከማስታወቂያ እና ከሚያከራያቸው ቤቶች ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ተችሏል። ትልቁ የፌዴሬሽኑ ስኬት የሚባለው የሊግ ኩባንያ እንዲመሠረት ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ መስዋትነት በመክፈል ሊግ ኩባንያው እዚህ ቁመና ላይ ደርሶ ማየት ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ኩራት ይሰማዋል።” ብለዋል። “በቀጣይ የፌዴሬሽኑ አደረጃጀት አሰራር ማዘመን፣ የወጣቶች እና የሴቶችን እግርኳስ ልማት ማስፋት፣ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን እንዲኖር ማድረግ ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነታችን አጠናክረን መቀጠል እና የፌዴሬሽን ገፅታን በሚገባ ለማስተዋወቅ፣ ጠንካራ የህዝብ ግኑኝነት በመፍጠር የመረጃ አሰጣጣችንን ማዘመን በቀጣይ የምንሰራቸው ሥራዎች ናቸው” ሲሉም አክለው ተናግዋል።

በመቀጠል ድምፅ የሚቆጥሩ አካላትን የመምረጥ ሥራ ተካሂዶ የጉባዔውን አጀንዳ እንዲያፀድቁ ተሳታፊዎች በአብላጫ ድምፅ ካፀደቀ በኃላ በአቶ ባህሩ ጥላሁን አማካኝነት በ2012  ፌዴሬሽኑ ያከናወናቸውን ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርትን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን አብዛኛውን ከላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ተሰሩ ካሏቸው ዋና ዋና ሀሳቦች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ቢሆንም የተለዩ ሊባሉ የሚችሉት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው :-

* የብሔራዊ ቡድን የሚመራበት ማንዋል ማዘጋጀት

* የውድድር መተዳደርያ ደንብ ማዘጋጀት

* ውድድሮች በስፖርታዊ ጨዋነት እንዲካሄዱ ማድረግ መቻሉ

* 11ኛውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ማድረጉ

*የደጋፊዎች ጥምር ጉባዔ መፍጠር

* ስልጠናዎችን በተመለከተ ለአሰልጣኞች፣ ለዳኞች፣ ለጨዋታ ታዛቢዎች መጠነ ሰፊ የሆነ ስልጠናዎችን መስጠት (ይህን በቁጥር ዘርዘር አድርገው አስቀምጠዋል)

* ለክልል እግርኳስ ፌዴሬሽኖች የ2.8 ሚሊዮን ብር የገንዘበ ድጎማ ማድረግ

* ፌዴሬሽኑ ወቀሳ ሲቀርብበት የቆየውን የሆቴሎች እዳን ሙሉ ለሙሉ መክፈል ችሏል። 

*በተለያዩ የእድሜ እርከኖች የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ማከናወን 

አስከትለው ድክመቶች ያሏቸውን ነጥቦች በለተመለከተ ተከታዩን ነጥብ አቅርበዋል።

* የፍትህ አካላት ውሳኔ መዘግየት

* ከ17 ዓመት በታች የፕሪምየር ሊግ ውድድር አለማካሄድ

* ከዩኒቨርስቲ መምህራኖች ጋር የተጀመሩ የታዳጊዎች ሥልጠና ውጤታማ አለመሆን

* የተሰሩ ሥራዎችን ሪፖርት ለሚመለከተው አካላት የማድረስ ባህል አለማዳበር ካሉ በኃላ የበጀት እጥረት ፌዴሬሽኑ እንዳጋጠመው ገልፀው በዋናነት የዋልያ ቢራ ፋብሪካ በኮቪድ ምክንያት ክፍያውን ማቆም አንዱ ችግር እንደሆነ ገልፀዋል።

ከአቶ ባህሩ በ2012 የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር ካቀረቡ በኃላ በቀረበው ሪፖርት ዙርያ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን ወደ ማዳመጥ ቢያመራም አብዛኛው የጉባዔው ጠያቂዎች ተመሳሳይ የሆኑ ሀሳብ ያነሱ በመሆኑ የተለየ ያቀረቡትን ስንመለከት የመጀመርያው ተናጋሪ የሆኑት የተጫዋቾች ማሕበር ፕሬዝደንት የሆኑት አሰልጣኝ ዮሐንሰ ሳህሌ ተከታዮን ጥያቄ አቅርበዋል።

— የዲሲፕሊን ኮሚቴ የሀገሪቱን ህገ መንግስት በሻረ ሁኔታ የኮሚቴው አባላት አይጠየቁም፣ አይከሰሱም የሚለው መመርያ ተገቢ አይደለም ?

– ሦስቱ መቀመጫቸውን ትግራይ ያደረጉ ቡድኖች በዚህ ዓመት የማይሳተፉ ከሆነ በቡድኖቹ ውስጥ ያሉ ሦስት መቶ የሚጠጉ ተጫዋቾች ያለ ሥራ ሊቀመጡ ነው። ይህ ደግሞ ተጫዋቾችን ቤተሰቦችን ብዙ አካላትን ሥራ የሚያሳጣ እና ከፍተኛ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ወደ ሌላ ክለብ የሚያመሩበትን ሁኔታ እንደ መፍትሄ ምን ያሰበው ነገር አለ?  

– የአሰልጣኞች ስልጠና ከቆመ አምስት ዓመት ሆኖታል። ይህ እንዴት ይታያል? የቴክኒክ ኮሚቴው ያለበት ቁመና ምን ይመስነበረበት።

– የዲሲፕሊን አባል ሁለት ዓመት መስራት አለበት እያለ 13 ዓመት የሰሩ ዲሲፕሊን ኮሚቴን ቤታቸው ያደረጉ አሉ። እዚህ ላይ ምን ታስቧል።

አቶ ሙሉጌታ (ከአማራ ክልል ተወካይ)

– ሪፖርቱ በጥሩ መንገድ የቀረበ ቢሆንም የክልል እግርኳሶችን ያማከለ አይደለም። የክልሎች የስራ ሪፖርት ያካተተ ቢሆን? 

– የዲሲፕሊን ኮሚቴ የውሳኔ መዘግየት ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ ውሳኔ የመስጠትም ችግር አለ? 

አቶ ፈለቀ ዋቄ (ከአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን) 

– ባለሙያዎች በተለይ ዳኞች አቅማቸውን እንዲያዳብሩ በምናዘጋጀው ስልጠና ለአሰልጣኝ ኢንስትራክተሮች በቀን ዘጠኝ መቶ ብር እንድንከፍል የምንጠየቅበት መንገድ መታሰብ አለበት። የክልል ፌዴሬሽኖችን አቅም የሚፈታተን በመሆን ፌዴሬሽኑ ቢያጤነው?

-በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17ዓመት በታች ውድድር አለማካሄዱ እንደ ድክመት ቢቀርብም በክልሎች እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች በሪፖርቱ መቅረብ አለበት። ለምሳሌ አዲስ አበባ ከ17 ዓመት በታች ውድድር በሁለት ምድብ ተከፍሎ ማካሄዱ መቅረብ ነበረበት።

በቀረበው ጥያቄ ዙርያ አቶ ኢሳይያስ ጅራ ምላሽ ስጥተዋል። 

– ዲሲፕሊን ኮሚቴ በተመለከተ ምርጫ ያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው እንደሆነ እና የማገልገል ዘመኑ አራት ዓመት ነው። የዲሲፒሊን ኮሚቴው ስራው ፈታኝ ነው የሚዘገይበትም ምክንያት እናተው ክለቦች ያለ ደንብ እና መመርያ ባለማወቀው ተጫዋቾችን ታሰናብታላችሁ። ይህ ጫና ፈጥሯል። በየውድድሩ የሚታዩ የዲሲፕሊን ውሳኔ የሚፈልጉ እንዳለ ሆኖ እንደገና የተጫዋቾች እና የክለብ ቅሬታዎችን ማስተናገድ ሥራውን አብዝቶባቸዋል።  የፍትህ አሰጣጥ ውሳኔ ላይ ችግር የለም አንልም። ግን መመርያውን ማወቅ ያስፈልጋል። የሚዘገየውን ለማስቀረት ወደ ሊግ ኮሚቴዎች በማውረድ ለማስተካካል አደረጃጀቶችን እየሰራን ነው። 

– ስልጠናን በተመለከተ እውነት ነው ስልጠና እየተሰጠ አይደለም። ያለውን ሁኔታ ታውቁታላችሁ። ከካፍ የመጣ መመርያ ነው። ይህን ከካፍ ጋር በመነጋገር ለማስተካከል ይሞከራል። የቴክኒክ ኮሚቴውም አደረጃጀት መስተካከል ያለባቸው ሁኔታዎች አሉ እርሱ ላይ ስራ እንሰራለን። በአዲስ አበባ በኩል የቀረበው የኢንስትራክተር ክፍያ ዙርያ ተገቢ ነው በቀጣይ የምንመለከተው ይሆናል።

– በትግራይ ክለቦች ዙርያ አሰልጣኝ ዮሐንስ ያነሳው ጉዳይ ተገቢ ነው። እኛም በአመራር ደረጃ የተነጋገርንበት ጉዳይ ነው። ወደ ጉባዔው መጠናቀቂያ ላይ የደረስንበትን ድምዳሜ የምናሳውቀው ይሆናል። በመጨረሻ ከጉባዔው የወሰድናቸው ተቃሚ ግብአቶች አሉ እርሱን ወስደን በቀጣይ የምንሰራቸው ይሆናል።

በመጨረሻም በቀረበው ሪፖርቱ ላይ ድምፅ እንዲሰጥበት ተደርጎ ጉባየተኛው ያለ ተቃውሞ በሙሉ ድምፅ ፀድቆታል። ወደ ሻይ ፕሮግራም ያመራ ሲሆን ከሻይ መልስ የ2013 እቅድ ዙርያ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል

© ሶከር ኢትዮጵያ