የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 12ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የከሰዓት ውሎ

ከዚህ ቀደም ከነበሩ ጠቅላላ ጉባዔዎች አኳያ በሁሉም ረገድ የተሻለ ውይይት የተካሄደበት እና ጤናማ የነበረው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔ በስኬት ተጠናቀቀ።

ረፋድ ላይ አብዛኛው ጤናማ በሆነ እና ሥርዓቱን ጠብቀ መንገድ የተካሄደው 12ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተመሳሳይ ከሰዓት በተካሄደው ውሎም መልካም የሚባል ነበር። ከሻይ መልስ ቀጥሎ የፈዴሬሽኑ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ነብዩ ደምሴ የ2012 የሒሳብ ሪፖርት በዝርዝር አቅርበዋል።

ፌዴሬሽኑ ከተለያዩ መንገዶች ያሰባሰባቸውን ገንዘቦች ምንጩ እና የገንዘቡ መጠን ከገለፁ በኋላ በአጠቃላይ የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን 121,446,564.32 ብር እንደሆነ ገልፀው  ፌዴሬሽኑ ለብሔራዊ ቡድን ለውድድሮች፣ ለወዳጅነት ጨዋታዎች እና ለተለያዩ የሥራ ማስኬጃዎች የወጡ አጠቃላይ ወጪዎች 121,714,357.28 ሚሊየን ብር ወጪ ሲደረግ ከወጪ ቀሪ ልዩነት 19,732,207.04 መሆኑን ገልፀዋል።

በማስከተል ወደ ጥያቄ እንዲያመራ የመድረኩ መሪ ለጉባዔተኛው እድል ቢሰጡም ተሰብሳቢው ምንም አይነት ጥያቄ ባለማቅረቡ አቶ ኢሳይያስ ጅራ ቀጥለው በሰጡት አስተያየት “ፌዴሬሽኑ ከዕዳ ተላቆ በዚህ ሁኔታ አቅሙን ማደራጀቱ ፌዴሬሽኑ በመልካም የሚባል የፋይናንስ አቅም ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው። ለዚህም ለፋይናስ ክፍሉ ምስጋና አቀርባለው ። በቀጣይም የፋይናስ አቅማችንን ከዚህ በተሻለ ከስፖንሰር ገቢ ለማስገኘት ይሰራል።” ብለዋል። በመቀጠል አቶ ደረጄ ኦዲት ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን እንደ ድክመት ፌዴሬሽኑ የገዛውን ህንፃ ስም ወደ ራሱ አለመዞሩ ከማድረጉ በቀር አብዛኛው የገንዘብ አወጣጡና ገቢው ጤናማ መሆኑን ከገለፁ በኃላ ባቀረቡት የፋይናንስ እና የኦዲት ሪፓርቱም ላይ ጉባዔው እንዲያፀድቀው ጥያቄ አቅርበው በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።  

በማስከተል ጉባዔው በልዩ አጀንዳ እንዲያየው አቶ ኢሳይያስ ጅራ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ለመመስረት ያቀረቡትን ጥያቄ በፌዴሬሽኑ መተዳደርያ ደንብ አንቀፅ 10ቁ 3 መሠረት ጠቅላላው ጉባዔው እንዲያፀድቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አባል እንዲሆን ጉባዔው በሙሉ ድምፅ አፅድቋል። የክልሉ ፌዴሬስን ተወካይ ሆነው የቀረቡት አቶ አንበስ አበበም መድረኩ ላይ ቀርበው የክልሉን እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስተዋውቀዋል።

ሌላው በተለየ አጀንዳ የታየው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ቡድን የሚሳተፉበትን ጉዳይ አስመልክቶ በተደጋጋሚ ጥያቄዎች እየቀረቡ መሆኑ ነው። ይሄን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ ሦስት ወር ባልበለጠ ጊዜ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚጠሩና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረን መመርያ በመውሰድ አቅጣጫ ከያዘ በኃላ ለጉባዔው የሚያቀርብ እንደሆነ አቶ ኢሳይያስ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ2013 በጀት ዓመት እቅድን አስመልክቶ አስቀድሞ ለጉባዔተኛው የታደለ በመሆኑ ከመድረኩ በቀጥታ ሳይቀርብ ከጉባየተኛው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች እንዲቀርቡ መድረኩ ክፍት የሆነ ሲሆን በዚህም መሠረት በርከት ያሉ አሻሚ ግልፅ ያልሆኑና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቢቀርቡም የተለየ ያልናቸውን ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው።

* የሜዳዎች በየአካባቢው እጥረት አለና ይህን ለማስተካከል ምን ታስቧል?

* የሴቶች እግርኳስን በተመለከተ ቡድኖች እየፈረሱ ነው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል

* በፓርላማ የፀደቀው የቢራ ፋብሪካዎች ስፖንሰር እንዳያደርጉ የወጣው አዋጅ በድጋሚ እንዲጤን መሠራት አለበት

* ፌዴሬሽኑ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ንግግር አድርጎ ትግራይ ላይ መቀመጫቸውን ያደረጉ ክለቦች የሚሳተፉበት እድል ቢመቻች የሚሉ ጥያቄዎችን ተነስተው አቶ ኢሳይያስ ጅራ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

– ሁሉም በሊግ ውድድር የሚሳተፉ ክለቦች የሴቶችን ቡድን እንዲይዙ አስገዳጅ ህግ እያመጣን ነው። እኛም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የክለቦችን አደረጃጀትን ወርደን በመፈተሽ እንሰራለን።

– የክልል ፌዴሬሽኖች ከ15 እና 17 ዓመት በታች እንዲሁም የሴቶችም ውድድር ግዴታ ማድረግ አለባችሁ። ውድድር አድርገናል ወይም አሳትፌያለሁ ለማለት ብቻ ሳይሆን በተደራጀ እና በተጠናከረ መልኩ ማድረግ አለባችሁ። በቀጣይ የምናዘጋጃቸው ውድድሮች ስላሉ ከወዲሁ ተዘጋጁ። የሚሉና ሌሎች ገንቢ የሆኑ ምላሾች ከሰጠ በኃላ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ የ2013 በጀት ዓመት እቅድን አፅድቆታል።

በማስከተል የጉባዔው የክብር አባላት የሆኑት አቶ ተካ አስፋው እና ወ/ሮ ጥሩወርቅ ያላቸውን መልዕክት እንዲያቀርቡ እድል የተሰጣቸው ሲሆን ሁለቱም ጉባዔው ከመቼው ጊዜው በተሻለ ጤናማ በሆነ መንገድ በጥሩ ሁኔታ መካሄዱን አድንቀው ይህ የሆነው አሁን ያለው የሥራ አስፈፃሚ አባል በፌዴሬሽኑ ውስጥ የፈጠረው ለውጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

በቀጣይ የሚካሄደው የፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ሀዋሳ ከተማ ላይ እንደሚካሄድ እና አጀንዳውም የጠቅላላ ጉባዔው መተዳደርያ ደንብን አስመልክቶ የተለያዩ ማስተካካያዎች ማድረግ ስላስፈለገ እንደ ሆነ አቶ ኢሳይያስ ጅራ አሳውቀዋል።

በመጨረሻም መቀመጫቸውን ትግራይ ክልል ያደረጉ ክለቦችን በተመለከተ አቶ ኢሳይያስ ሲያብራሩ የፌዴሬሽኑ አመራር ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከአስራ አራት ቀን በፊት እንደተነጋገረ ገልፀው ትናንት የመጨረሻ ውሳኔ መወሰናቸውን ገልፀዋል። በዚህም መሠረት ቡድኖቹ የማይሳተፉ ከሆነ ተጫዋቾቹ አሰልጣኞቹ ስራ መሥራት ስላለባቸው ክለብ የሚያገኙ ከሆነ ቢጫወቱ የሚል (የተለየ የዝውውር መስኮት እንደተዘጋጀ) ውሳኔ እንደተወሰነ እና ሁሉ ነገር ሠላም ሲወርድ ሦስቱ ክለቦች ወደ ቀድሞ ውድድር ከተመለሱ ተጫዋቾቹ ውል ያለባቸው ከሆነ ወደ ክለቦቻቸው እንዲመለሱ ሁለቱንም አካላት ለመጠበቅ ይሄን ውሳኔ አሳልፈናል። ሽረ አስራ ስድስት ተጫዋቾች  አሉን እንሳተፍ እያለ ቢሆንም ኃላፊነት የሚወስደው አካል ማነው የሚለው ጥያቄ መልስ ይፈልጋል ብለዋል።

በመጨረሻም የ2012 ዓመት 12ኛ የፌዴሬሽኑ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በስኬት ተጠናቋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ