ሦስት ግቦችን ያስተናገደው የፋሲል ከነማ እና ዩ ኤስ ሞናስቲር ጨዋታ በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ቢጠናቀቅም በድምር ውጤት ዩ ኤስ ሞናስትር ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።
የ2011 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊው ክለብ ፋሲል ከነማ የኮንፌዴሬሽን ካፕ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ስታዲየም አከናውኗል። በጨዋታውም ፋሲል ከነማዎች የተሻሉ ሆነው ሁለት ግቦችን ቢያስቆጥሩም ተጋባዦቹ ባለቀ ሰዓት ባስቆጠሩት የጭንቅላት ኳስ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ የቻሉበትን ውጤት ይዘው ወጥተዋል።
አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ከሳምንት በፊት ወደ ሞናስቲር በማቅናት ሁለት ለምንም ከተረቱበት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም በመጀመሪያው ጨዋታ ላይ የግራ መስመር ተከላካይ የነበረውን ሳሙኤል ዮሐንስን በአምሳሉ ጥላሁን እንዲሁም የአማካይ መስመር ተጫዋቹ ይሁን እንዳሻውን በበዛብህ መለዮ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።
ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ኳስን ተቆጣጥረው ሲጫወቱ የነበሩት ዐፄዎቹ በጨዋታው ጅማሮ በቶሎ ግብ አስቆጥረው ጨዋታው ላይ ያላቸውን መነሳሳት ለማሳደግ ሞክረዋል። በተቃራኒው በሜዳቸው ያገኙትን የ2-0 መሪነት አስጠብቀው ለመውጣት ሲታትሩ የነበሩት ሞናስቲሮች ብዙም የማጥቃት ፍላጎት ሳያሳዩ ጨዋታውን ቀጥለዋል። በ17ኛው ደቂቃ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን ኳስ ግን ወደ ግብነት ለመቀየር ጥረው መክኖባቸዋል።
የኳስ ቁጥጥር የበላይነታቸውን በውጤት ማጀብ የተሳናቸው ፋሲል ከነማዎች ከመስመር ላይ የሚነሱ ኳሶችን ሙጂብን ዒላማ በማድረግ ወደ ሳጥን ቢጥሉም ፍሬያማ መሆን አልቻሉም። ይህ ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከግራ መስመር እንዲነሳ የተደረገው በረከት ደስታ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን እንዲገባ እና ኳሶችን እንዲሞክር ሲታሰብም እስከ ግማሽ ሰዓት መዳረሻ ድረስ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ አልነበሩም። የመልሶ ማጥቃት እና የቆሙ ኳሶችን ባነሰ የማጥቃት ፍላጎት ሲጠቀሙ የተስተዋሉት ሞናስቲሮች በተለይ በ25ኛው ደቂቃ ለግብነት የቀረበ ሙከራ በጨዋታው አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር የተገኘን የቅጣት ምት ወደ ሳጥን አሻግረውት በጭንቅላት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር።
ጨዋታውን እና ኳስን ተቆጣጥረው አብዛኛውን ጊዜ የሞናስቲር ሜዳ ላይ ማሳለፍ የቀጠሉት ፋሲሎች 28ኛው ደቂቃ ላይ የልፋታቸውን ውጤት አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃ ላይም ሱራፌል ዳኛቸው በግራ መስመር የተገኘን የመልስ ውርወራ ተቀብሎ ወደ ግብ የመታው ኳስ በሞናስቲር ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ የትኩረት እና ቦታ አያያዝ ስህተት ጎል አስቆጥሮ ፋሲሎች መሪ ሆነዋል። ፋሲሎች ይህንን ግብ ካስቆጠሩ ከ10 ደቂቃዎች በኋላም በበዛብህ እና ሙጂብ የግንባር ኳስ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃረበው ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በዐፄዎቹ መሪነት ተጠናቋል።
የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በአንድ ደቂቃ ውስጥ የባለሜዳዎቹን ተነሳሽነት ለማክሸፍ ጥሩ እድል በቆመ ኳስ ያገኙት ሞናስቲሮች ያገኙትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቀርቷል። በተሰነዘረባቸው የመጀመሪያ ደቂቃ ሙከራ ያልተደናገጡት ፋሲሎች በጥሩ የኳስ ቅብብል መሪነታቸውን ወዲያው ከፍ አድርገዋል። በዚህም በ50ኛው ደቂቃ ሰዒድ ሀሰን ከቀኝ መስመር በጥሩ ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ ሙጂብ በግምባሩ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
በ52ኛው ደቂቃ የፋሲል ተጫዋቾች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅመው ሞናስቲሮች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ነገርግን ሚኬል ሳማኪ በጥሩ ቅልጥፍና ሙከራውን አምክኗል። ይህ ሙከራ በተደረገ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ዐፄዎቹ ድንቅ ኳስ ከሳጥን ውጪ ሞክረው ግብ ጠባቂው በሽር ቤን ሰዒድ አውጥቶታል። ሁለተኛውን ግብ ካስተናገዱ በኋላ በአንፃራዊነት በተሻለ ለመንቀሳቀስ የጣሩት ተጋባዦቹ የሚያገኟቸውን ኳሶች ድካም በተቀላቀለበት ስሜት ውስጥ በመሆን ወደ ጎልነት ለመቀየር ሞክረዋል። ነገርግን የቡድኑ የማጥቃት ሂደት በተደራጀ ሁኔታ የተቃኘ ባለመሆኑ እድሎችን በተደጋጋሚ መፍጠር ሳይችሉ ቀርቷል።
ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ እየሄደላቸው የሚመስለው ፋሲል ከነማዎች በዚህኛውም አጋማሽ ከኳስ ጋር ያላቸውን ጊዜ በማርዘም ጨዋታውን ቀጥሏል። በተለይ ግን ቡድኑ ከሱራፌል እግር የሚነሱ ኳሶችን በመጠቀም ተጨማሪ ግብ የማስቆጠሪያ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ነበር። በዚህኛው አጋማሽ የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ሞናስቲሮች በበኩላቸው በ68ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት እጅግ ጥሩ ኳስ የሚኬል ሳማኪ መረብ ላይ ለማሳረፍ ጥረዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ግማሽ ሰዓት ካስቆጠረ በኋላ የቅጣት ምት ያገኙት ሞናስቲሮች አጋጣሚውን ወደ ጎልነት ለመቀየር ሲጥሩ ፋሂም ቤን ረመዳን እና ሜኬል ሳማኪ በአሰቃቂ ሁኔታ ተጋጭተው በተከሰተ ከባድ ጉዳት ጨዋታው ከ10 በላይ ደቂቃዎች ተቋርጧል። እርስ በእርስ የተጋጩት ተጫዋቾችም በሁለት አምቡላንስ ተጭነው ለተሻለ ህክምና ከስታዲየሙ ወጥተዋል።
ጨዋታው ከተቋረጠበት ሲቀጥል ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ የነበረ ሲሆን በተጨመሩት 14 ደቂቃዎች ሁለቱ ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። በ90+5 ደቂቃም የተገኘን የመዓዘን ምት ፋዲ አፍሮዪ በግምባሩ ጎል አስቆጥሮ ሞናስቲሮች ወደ ቀጣይ ዙር የሚያልፉበትን ውጤት ይዘዋል። ውጥረቶች፣ ፍትጊያዎች እና ረጃጅም ኳሶች በበዙበት ቀሪ ደቂቃዎች ላይም ፋሲሎች ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። በተለይ ሙጂብ፣ ሱራፌል እና በዛብህ በግላቸው ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ጨዋታውም ተጠናቆ በድምር ውጤት ያሸነፈውን ዪ ኤስ ሞናስቲር ወደ ቀጣይ ዙር አሳልፏል።
3-2 በሆነ ድምር ውጤት መርሐ-ግብሩን ያሸነፉት ዩ ኤስ ሞናስቲሮች በቀጣይ በአንደኛ ዙር የኮንፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታውን አህሊ ትሪፖሊን ይገጥማሉ።
© ሶከር ኢትዮጵያ