በህይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምን ጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን እያሰብን እንገኛለን። ለዛሬ የመንግሥቱ ወርቁን የሜዳ ውጪ የሥራ ህይወት እንቃኛለን።
ማስታወሻ ፡ በገነነ መኩሪያ በመፅሀፍ መልክ የተዘጋጀው ከመንግስቱ ወርቁ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ ፣ ‘ይድረስ ለባለንብረቱ’ የሚለው በፋንታሁን ኃይሌ ፣ ኃይማኖት ቃኘው እና ተዘራ አለነ የተዘጋጀው መፅሀፍ እና በልሣነ ጊዮርጊስ ጋዜጣ መንግስቱ ወርቁ የተዘከሩባቸው ሕትመቶች ለዚህ ፅሁፍ ግብአትነት ተጠቅመናል።
መንግሥቱ ወርቁን በታላቅ እግርኳስ ተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት ሙያ ብቻ መግለፁ በቂ አይደለም። በዚህም የወጣቱን መንግሥቱ የተጫዋችነት ዘመን ከሜዳ ውጪ የነበረውን ህይወት መመልከት የታላቁን ሰው ሌላ ገፅታ እንድናስተውል ያደርገናል። የዚያን ዘመን እግርኳሰኞች ስፖርቱ የሙሉ ጊዜ ስራቸው አልነበረም። ልምምድ እና ጨዋታ የሚያደርጉት በትርፍ ጊዜያቸው ነበር። በመሆኑም ከእግርኳሱ ጎን ለጎን ህይወታቸውን ለመምራት ፣ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር በሌላ ሙያ ላይ ይሰማራሉ። በብዛት በሚጫወቱባቸው ክለቦች መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው ኑሯቸውን ይገፋሉ። መንግሥቱ ወርቁም በበኩሉ ከዚህ ቀደም እንዳስነበብናችሁ በነበረው የቴክኒክ ሙያ በመብራት ኃይል መሥሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ ነበር። ለጊዮርጊስ እየተጫወተ መብራት ኃይል ላይ ግብ በማስቆጠሩ ምክንያት በተጀመረ አለመግባባትም ድርጅቱን ለመልቀቅ ተገዷል። ከዚህ በኋላ ወደአሰልጣኝነት ህይወት እስከገባበት ጊዜ ድረስ ግን የንግድ ሥብዕና የነበረው ሰው መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ የስራ ዘመንን አሳልፏል።
ከመብራት ኃይል ከለቀቀ በኋላ በነበረው ጊዜ መንግሥቱ ምርጥ የማርኬቲንግ ባለሙያ ሆኖ ነበር። ይህንን ማድረግ የቻለውም ስራ ባጣበት ወቅት በእጁ የሚገኘውን ሀብት ማየት በመቻሉ ነበር። በጊዮርጊስ ተጫዋችነቱ ዝነኛ እና ብዙ ሰዎች ያውቁት የነበረ በመሆኑ ናይል ኢንሹራንስ ተከፍቶ ስራ በጀመረ ጊዜ በድፍረት ለመቀጠር ሄደ። “የምትፈልጉትን ደምበኛ አመጣላችኋላው ፤ ስራዬን አይታችሁ ደመወዝ ትከፍሉኛላችሁ።” በማለት በልበሙሉነት ያቀረበውን ሀሳብ ድርጅቱ ተቀበለው። በ150 ብር ደመወዝ በጀመረው ስራም በአጭር ጊዜ ውስጥ ደመወዙ 2000 ብር ሲገባ በሚያመጣው ደምበኛ ብዛት ደግሞ ከፍተኛ የኮሚሽን ተከፋይ መሆን ቻለ። ከዚህም በላይ መስሪያ ቤቱ ሰዓት ፣ ወርቅ አልፎ ተርፎም መኪና ጭምር ሸለመው። ከዚህ በተጨማሪ ሚቸልኩትስ የተባለ ኩባንያ አዲስ ያስገባቸውን መኪኖች ለህዝቡ ያስተዋወቀው እና ከፍተኛ ሽያጭ ያገኘው በመንግሥቱ አስተዋዋቂነት ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን መንግሥቱ በኳስ ተጫዋችነቱ ሜዳ ላይ አልሰነፈም። ከሜዳ ውጪ የገጠመው ሀብት ይበልጥ ጠንካራ ሰራተኛ እንዲሆን አዳረገው እንጂ የገንዘብ እና የወጣትነት መገጣጠም የሚያመጣው ጣጣ ሰለባ አልሆነም።
ቀጣዩ የመንግሥቱ የስራ ህይወት ከማርኬቲንግ ባለሙያነት አልፎ በራሱ የቆመ ሙሉ የንግድ ሰው ብሎም በስሩ ሰራተኞችን ቀጥሮ የሚያሰራ ነጋዴ መሆን ነበር። ከኢንሹራንስ ስራው የሚያገኘውን ገንዘብ በመቆጠብ ወደ ነዳጅ ማደያ ስራ ውስጥ ገባ። ዛሬም ድረስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘውን ነዳጅ ማደያ በ60,000 ብር በመግዛት አሁንም ዕውቅናው ያመጣለትን የሰው ሀብት ወደ ገንዘብ በመቀየሩ ቀጠለ። በዚህም በእግርኳስ ሜዳ ጀብዱዉ የሚወዱት ባለመኪኖች ቋሚ ደምበኞቹ ወደ ማደያው ይጎርፉ ጀመር፡፡ በእርግጥም ያለው ተወዳጅነት በርካታ ደንበኞችን አፍርቶለት የጀመረው ንግድ ፍሬ ማፍራት የጀመረው ወዲያውኑ ነበር። በዚህ የተለየ የህይወት መንገድ የታላቁን ሰው የንግድ ስብዕና (Business personality) በደንብ መገንዘብ ይቻላል። ከስር ጀምሮ መስራት ፣ መቆጠብ እና ኢንቨስትመንት ረጅም ጊዜ የሚወስዱ እና ውስብስብ ጉዳዮች ቢሆኑም እንደመንግሥቱ ላሉ ብሩህ ሰዎች ግን ቀላል ነበሩ። ነገሮች በዚህ ሁኔታ ቀጥለው መንግሥቱ ከልምምድ መልስ ማደያውን እያስተዳደረ እና ደንበኞቹን እየተንከባከበ ሽያጩን በመጨመር ላይ ሳለ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ።
በስራ ላይ በነበረበት በአንዱ ዕለት አንድ አሜሪካዊ መኪናው ቤንዚን ይጨርስና እያስገፋ ወደ ማደያው ይመጣል። ሆኖም ቤንዚን ቢሞላላትም መኪናዋ ልትነሳ አልቻለችም። ሰውየው ደግሞ የቀጠሮው ሰዓት ደርሶበት ስለነበር የሚያደርገው ነገር ይጠፋዋል። መንግሥቱ የሰውየውን ጭንቀት በማየት የራሱን መኪና ሰጥቶት ወደ ጉዳዩ እንዲሄድ ያደርገዋል። መኪናውንም አስጠግኖ ያረፈበት ሒልተን ሆቴል ድረስ ወስዶም ያስረክበዋል። በዚህ መልካም አድራጎቱም ከሰውየው ጋር መግባባት ቻለ። ያ አሜሪካዊ ከአንድ ዕለት አጋጣሚ በላፈ ለመንግሥቱ ቀጣይ የንግድ ስራዎች ትልቅ በር የከፈተ ሰው ነበር። “ይሄ ሰውዬ አሜሪካ ውስጥ የታወቀ ቢዝነስ ማን ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ንግድ ለማስፋፋትና ወኪሎች ለማነጋገርና ለማሠራት ነበር የመጣው። በአጠቃላይ ሰውየው ብዙ ነገር የሚሰራ ነው፡፡ በነጋታው ስሄድ ስለእኔ አጣርቶና ተደንቆ ኳስ ተጫዋች መሆኔን እዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ስም እንዳለኝ ስለተገነዘበ ያቺም የሰራሁለት ውለታ ስላለች ‘በል እንግዲህ ጥሩ አጋጣሚ ነው የተገናኘነው ጥሩ የቢዝነስ ማን ከሆንክ እኔ ብዙ ነገር አሰራሃለሁ፡፡ በአጋጣሚ ጥሩ ፐርሰናሊቲ ያለው ሰው ወኪል እፈልጋለሁ። ገንዘብ ብድር የምታገኝበትን መንገድም አመቻችልሃለሁ’ አለኝ” በማለት መንግሥቱ የሰውየውን ማንነት ለሊብሮ ገልፆለት ነበር። ይሄኛው አጋጣሚ ደግሞ የመንግሥቱ ወርቁን የንግድ ተግባቢነት (Business communication) ችሎታ በሚገባ የሚመሰክር ነው።
ከአሜሪካዊው ሰው ጋር በመሰረተው ግንኙነት በመጀመሪያ የመኪና ማጠቢያ እቃዎች አስመጪነት ስራ መስራት ጀመረ በመቀጠልም በሚዮኖች የሚገመት ኢንቨስትመንት ውስጥ ለመግባት መንገድ ጀመረ። በሰውየው አማካይነት ከውጪ በተፈቀደለት ብድር የመጀመሪያው ስራ ዕቅድ የውሾች ምግብ ማቀነባበሪያ በመክፈት ወደ ውጪ ኤክስፖርት ማድረግ ነበር። ይህንንም በማድረግም በአህጉሪቷ የመጀመሪያው ሊሆን ይችል ነበር። በተጨማሪም ሌሎች አራት ዓይነት ሰፋፊ የንግድ ስራዎችን ለመጀመር አርባምንጭ አካባቢ ሰፊ ቦታ ተረክቦ በማስመንጠር ወደ ስራ ለመግባት ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር። አጠቃላይ የስራዎቹ ትርፍ ወደ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመትም ነበር። ከግማሽ ክፍለዘመን በፊት 5 ሚሊዮን ብር ምን ማለት እንደነበር መገመት መቼም ቀላል ነው። በዚህ ደረጃ ሰፊ ስራ ለመጀመር ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰው በዚያው ጊዜ በሜዳ ላይ ትልልቅ ታሪኮችን ይሰራ የነበረ እግርኳስ ተጫዋች መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል።
የመንግሥቱ ህልም ዕውን እንዳይሆን ሀገር ውስጥ የነበረው ቢሮክራሲ አንዱ ምክንያት ቢሆንም ለስድስተኛው አፍሪካ ዋንጫ ሽንፈት ቂም ተይዞበት የነበረ መሆኑም የራሱ ድርሻ እንደነበረው መንግሥቱ በቃለመጠይቆች ላይ ጠቁሞ አልፏል። የሆነ ሆኖ ሥራዎቹ ከመጀመራቸው በፊት ሀገራችን አቢዮት በመፈንዳቱ ከአሜሪካኖች ጋር መስራት የማይታሰብ ሆነ። መንግሥቱ እስከዚያ ድረስ ያፈራው ሀብትም ተወረሰበት። ይህ በመሆኑም ነበር መጀመሪያም ትልቅ ወዳደረገው እግርኳስ ፊቱን መልሶ ወደ አሰልጣኝነት ህይወት ውስጥ የገባው። ዕቅዶቹ ሰምረው የነበረ ቢሆንስ ? ገና በዚያ ዘመን ሀብቱን ወደ ሚሊዮኖች አሳድጎ በሀገር ብቻ ሳይሆን በአህጉር ደረጃ ከሚጠሩ ኤክስፖርተሮች መካከል የሚጠቀስ ሰው ቢሆን ኖሮ ቀጣዩን የአሰልጣኝነት ህይወቱ ይታሰብ ነበር ?
ይህ የመንግሥቱ ወርቁ የህይወት ክፍል በአማተር እግርኳስ ተጫዋችነቱ ያሳለፈው ቢሆንም አሁን ላይ ላሉ ፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋቾቻችን የሚሰጠው ትምህርት እንዳለ ዕሙን ነው። ልክ እንደኳሱ ሁሉ መንግሥቱ በሁሉም ረገድ ጠንካራ ሰራተኛ እና የገንዘብ አያያዝ አዋቂ እንደነበር መረዳት ብቻውን ተጫዋቾቻችን ከሜዳ ውጪ ባለው ህይወታቸው ነገን በትልቁ የሚያሙ ባለርዕዮች እንዲሆኑ ያመላክታል እንላለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ