የዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የትግራይ ክልል ክለቦች ስለመወዳደራቸው እርግጥ አለመሆኑን ተከትሎ በ13 ክለቦች መካከል የሚደረግ አማራጭ ድልድል ወጥቷል።
የ2013 የኢትዮጵያ ቢትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የፊታችን ቅዳሜ ታኅሣሥ 3 በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚደረጉ ሁለት መርሀግብሮች በይፋ ይጀመራል፡፡ ውድድሩ ከቀናት በፊት እንደሚጀመር ይፋ በሆነበት ወቅት ሊጉ እንደተለመደው በአስራ ስድስት ክለቦች መካከል ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም በትግራይ ክልል አካባቢ ከተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር በክልሉ የሚገኙ መቐለ 70 እንደርታ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ይሳተፋሉ ወይንስ አይሳተፉም የሚለው ጥያቄ ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ በዚህም መሠረት ቀደም ብሎ ከወጣው ድልድል በተለየ የሦስቱ መውጣት እርግጥ ከሆነ የሚከናወንበት አዲስ መርሐ ግብር ወጥቷል።
በአዲሱ ድልድል መሠረት የዓመቱ ጨዋታዎች ወደ 156 ዝቅ የሚል ሲሆን የመጀመሪያ ስድስት ሳምንታት ጨዋታዎችም በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከወናሉ።
የሊግ ካምፓኒው ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ክለቦቹ ስለመሳተፋቸው እስከውድድሩ መጀመርያ ቀን ድረስ ማረጋገጩ ከሰጡ እንደሚሳተፉ ገልፀው የነበረ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት የተሳትፏቸው ጉዳይ አጠራጣሪ የሆኑት ሦስቱ ክለቦች እጣፈንታ የሚለይ ይሆናል።
አዲስ በወጣው አማራጭ ድልድል መሰረት የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታዎች
ቅዳሜ ታኅሣሥ 3 ቀን 2013
4:00 ሰበታ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ
9:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ፋሲል ከነማ
እሁድ ታኅሣሥ 4 ቀን 2013
4:00 ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልቂጤ ከተማ
9:00 ጅማ አባ ጅፋር ከ አዳማ ከተማ
ሰኞ ታኅሣሥ 5 ቀን 2013
4:00 ወላይታ ድቻ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
9:00 ባህር ዳር ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
አራፊ ቡድን – ሀዋሳ ከተማ
© ሶከር ኢትዮጵያ