የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከብሩክ በየነ ጋር

በብዙዎች ተስፋ የተጣለበት የዛሬው እንግዳቸን ብሩክ በየነ የተወለደው ከአዲስ አበባ 273 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ በምትገኘው ሀዋሳ ከተማ ነው። በመሀል ከተማው ልዩ ስሙ ቀበሌ 03 እየተባለ በሚጠራው ሰፈርም እድገቱን እንዳደረገ ይናገራል። ከልጅነቱ ጀምሮ የኳስ ፍቅር በውስጡ የነበረው ብሩክ የጨርቅ ኳሶችን እየሰራ በሰፈሩ ይጫወት ነበር። እድሜው ከፍ ሲልም በአሁኑ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አሠልጣኝ ተመስገን ዳና ለመገራት ወደ ፕሮጀክት ቡድን አመራ። በዚህ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ለ2 ዓመታት ቢጎለብትም ከመኖሪያ ቤቱ ራቅ ስለሚል ከ2 ዓመት በላይ አሠልጣኝ ተመስገን ጋር መቆየት አልቻለም። ይልቁንም ለሠፈሩ ቅርብ የነበረውን ህይወት ብርሃን የተባለ ሌላ የፕሮጀክት ቡድን ተቀላቅሎ በድጋሜ ለ2 ዓመት ራሱን አሳደገ።

በሁለት የተለያዩ የፕሮጀክት ቡድኖች ራሱን በደንብ ያበቃው ተጫዋቹ በየዓመቱ ክረምት ሀዋሳ ላይ በሚደረገው የቄራ ካፕ ውድድር ላይ ይሳተፍ ጀመር። በዚህ ውድድር ላይ ጥሩ ብቃቱን በማሳየቱም 2009 ላይ ለሀዋሳ ከተማ የተስፋ ቡድን ለመጫወት የሙከራ እድል አገኘ። ሙከራውን እያደረገ ባለበት ጊዜም አሠልጣኝ አዲሴ ካሳ የተጫዋቹን ብቃት በፍጥነት በመረዳት ሀዋሳዎችን ቀድሞ ወደ ወልቂጤ ከተማ ወሰደው። በወልቂጤ ቤት ለሁለት ዓመታት ቆይታን ካደረገ በኋላም ድጋሚ አሠልጣኝ አዲሴን ተከትሎ 2011 ላይ ወደ ትውልድ ከተማው ሀዋሳ ተመለሰ። ያለፉትን ሁለት ዓመታትም በሀዋሳ ከተማ ቤት በዋና እና መስመር አጥቂነት ድንቅ ግልጋሎቱን እየሰጠ ይገኛል።

ከቀናት በፊት በተጠናቀቀው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እንዲያገለግል በአሠልጣኝ ተመስገን ዳና ጥሪ የደረሰው ተጫዋቹ በውድድሩ ላይም ሁለት ኳሶችን ከመረብ አገናኝቶ የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ቆይታውን በግሉ በስኬት ጀምሯል። በሴካፋው ውድድር ላይም ሆነ በሀዋሳ እና ወልቂጤ ቆይታው ጥሩ ተጫዋች መሆኑን እያስመሰከረ ያለው ባለ-ተሰጥኦ ብሩክ በየነ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል።


የእግርኳስ አርዓያህ ማነው?

ጌታነህ ከበደ። በፊት እርሱ ደቡብ ፖሊስ ሲጫወት የቡድኑ ካምፕ (ማረፊያ) እኛ ሠፈር ነበር። ክለቡም በአቅራቢያችን ስለሚገኝ እኔን ጨምሮ በርካታ የሠፈራችን ልጆች የደቡብ ፖሊስ ደጋፊዎች ነበርን። ይህንን ተከትሎ የክለቡን ጨዋታዎች ለማየት ሁሌ ሜዳ እንሄድ ነበር። ቡድኑም እንዲያሸንፍ እርሱ ጎል ሲያስገባ በጣም እንደሰት ነበር። ከዚህ መነሻነት እርሱን እያየው ስለነበር እንደ አርዓያ የምጠቅሰው ጌታነህን ነው። 


ኮሮና ከመጣ በኋላ አዲስ የለመድከው ወይንም እየለመድክ ያለኸው ልማድ አለ?

ቤት መሆን ለእኔ አዲስ ልማድ ነው። እንደሚታወቀው ኳስ ተጫዋች ብዙ ጊዜ ውድድር አልያም ዝግጅት ላይ ስለሚሆን ቤት ብዙም ጊዜ አይኖረውም ነበር። ዓምና ኮቪድ ከመጣ በኋላ ግን ሁለቱም ነገሮች ስለሌሉ ቤት መሆንን ለምጃለው። እርግጥ በግሌ እየወጣሁ ልምምድ ብሰራም አብዛኛውን ጊዜ ቤት ነበርኩ። ስለዚህ ከኮሮና በኋላ አዲሱ ልማድ ቤት መሆንን መልመድ ነው።


ኮቪድ-19 አሁን ጠፍቷል የሚል ሠበር ዜና ብትሰማ መጀመሪያ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው?

በነገራችን ላይ ይህንን ዜና መስማት በጣም ናፍቆኛል። ልክ ዜናውን እንደሰማው ወዲያው የማደርገው ነገር በጣም የሰለቸኝን ማስክ ቀዶ መጣል ነው። 

በእግርኳስ ህይወትህ ጥሩ ጊዜን ያሳለፍክበት የውድድር ዓመት መቼ ነው?
ዓምና በጣም ድንቅ ጊዜ ነበረኝ። ኮቪድ ተከስቶ ሊጉ ተቋረጠ እንጂ በግሌ ምርጥ የውድድር ዓመትን እያሳለፍኩ ነበር። እንደምታቀውም 9 ጎሎችን አስቆጥሬ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየተፎካከርኩ ነበር። 

እስቲ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችህን ራስህ ንገረኝ?

የሚጎላው ጠንካራ ጎኔ አልሸነፍ ባይነቴ ይመስለኛል። ደካማ ጎኔ ደግሞ አንድ ጎል አግብቼ የምረካው ነገር ነው። በጨዋታ ላይ ቀድሜ ጎል አግብቼ ሌላ ጎል ለመድገም አልበረታታም ነበር። ይህ ድክመት ነበረብኝ። ነገርግን ከዓምና ጀምሮ ይህንን ድክመቴን ለማሻሻል እየተጋሁ ነው። ለውጦችም ደግሞ አሉ።
ብሩክ እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን በምን ሙያ እናገኘው ነበር?

ይህንን ፈጣሪ ነው የሚያውቀው። የቀለም ትምህርቴንም ለኳስ ብዬ አቁሜ ነበር ወደ ወልቂጤ የተጓዝኩት። ነገርግን አሁን ላይ ዝም ብዬ ሳስበው ሹፌር የምሆን ይመስለኛል። አላቅም ግን በምን ምክንያት እንደሆነ ይህንን ያሰብኩት።
አንተ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ነህ። ስለዚህ ብዙ ተካላካዮችን በተቃራኒ ትፋለማለህ። በእስካሁኑ የእግርኳስ ህይወትህ የፈተነህ አልያም የከበደህ ተከላካይ አለ?
ልክ ነው የፈተነኝ አንድ ተከላካይ አለ። በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ዘንድሮ የእኛን ቡድን ተቀላቅሏል። እርሱም ምኞት ደበበ ነው። እስካሁን በተቃራኒ ሲፈትነኝ ነበር። አሁን ግን እኔ ያለሁበት ቡድን ስለገባ የሚፈትነኝ ልምምድ ሜዳ ላይ ብቻ ነው።


ከማንስ ጋር ተጣምረህ መጫወት ትፈልጋለህ?

ምን ጥያቄ አለው፣ ከጌታነህ ከበደ ጋር ነዋ (ጥያቄውን ገና ሳያል ፈጥኖ)። ቀድሜ እንዳልኩትም ጌታነህን እንደ አርኣያ ስለሆነ ስመለከተው የነበረው ከእርሱ ጋር ተጣምሬ መጫወት የሁል ጊዜም ህልሜ ነው።


ምርጫ ላይ እንምጣ። በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ከሚገኙ ተጫዋቾች የብሩክ ምርጡ ማነው?

ከቡድንህ ጠራህ እንዳልባል እንጂ መስፍን ታፈሰ ለእኔ ምርጡ ተጫዋች ነው። 


ይህንኑ ጥያቄ ወደ አሠልጣኞች እንውሰደው። ከአሠልጣኞችስ?

ከአሠልጣኝ አዲሴ ካሳ ጋር ለረጅን ጊዜ አብሬ ሰርቻለሁ። በእርሱ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ። ስለዚህ የእኔ ምርጡ አሠልጣኝ አዲሴ ካሳ ነው።


አሁን ደግሞ ሁለት ጥያቄዎችን ከአጋጣሚዎች ጋር አያይዤ ልጠይቅህ። በቅድሚያ በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበት አጋጣሚን አውጋኝ?

አጋጣሚዎቼ ከጨዋታ ጋር የተገናኙ ናቸው። በጣም የተደሰትኩበትም ጨዋታ ዓምና ፋሲል ከነማ ሁለት ጎሎችን አግብቶብን እየመራን ከኋላ ተነስተን ሦስት ለሁለት ያሸነፍንበት ጨዋታ ነው። ከመመራት ተነስተን ያሸነፍነው ጨዋታ ስለሆነ በጣም ነበር የተደሰትኩት። እኔም ደግሞ በጨዋታው የተነሳሳንበትን የመጀመሪየሰ ጎል አስቆጥሬ ነበር።


በተቃራኒ የተከፋህበትስ አጋጣሚ?

ይህም አጋጣሚ ከጨዋታ ጋር የተገናኘ ነው። እርሱም ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታን ገጥመን 5-1 በሆነ ውጤት የተሸነፍንበት ነው።


እርግጥ ገና ቢሆንም እግርኳስ ካቆምክ በኋላ በምን ሙያ የምትቀጥል ይመስልሃል?

ነጋዴ የምሆን ይመስለኛል። 


ወደ አሠልጣኝነት የመግባት ፍላጎት የለህም?

አለኝ። ነጋዴ ከመሆኔ በፊትም አሠልጣኝነትን እሞክራለሁ። የወደፊቱን አላቅም እንጂ አሁን ላይ አሠልጣኝ የመሆን ትንሽ ፍላጎት አለኝ። ይህ ካልተሳካልኝ ግን ወዲያው ወደ ንግዱ ዓለም እገባለው።


ብሩክ ቅፅል ስም አለህ አደል?

አዎ። አቡሌ ይሉኛል። ይህ ቅፅል ስም ገና ጨቅላ እያለው የወጣልኝ ነው። ማን እንዳወጣልኝ እራሱ አላቅም። ግን ቤት ውስጥ ነበር አቡሌ እየተባልኩ መጠራት የጀመርኩት። አሁን ላይም በርካታ ጓደኞቼ አቡሌ እያሉ ነው የሚጠሩኝ። እንደውም ብሩክ ሲባል የማያቁኝም አሉ።


እግርኳስ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች የአንተ የቅርብ ጓደኛህ ማነው?

ወንድማገኝ ማዕረግ ነው የእኔ የቀረበ ጓደኛ። ከወንድማገኝ ጋር አንድ ሠፈር ነን። አብረንም ነው የተማርነው። በተጨማሪም አሁን ላይ አብረን ነው በሀዋሳ ከተማ ያለነው። ከዚህ መነሻነት ከእርሱ ጋር በጣም ተቀራርበናል። 
ከእግርኳስ ውጪ ምን የተለየ ተሰጥኦ አለህ?
ከእግርኳስ ውጪ ምንም የተለየ ነገር የለኝም። ኳስ መጫወት ብቻ ነው የእኔ ተሰጥኦ።


በስተመጨረሻ ማለት የምትፈልገው ነገር አለ?

በእኔ የእግርኳስ እድገት አስትዋጾ ያበረከቱትን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለው። በተለይ አዲሴ ካሳ እድሜ እና ጤና እንዲሰጠው እመኛለው። ተመስገን ዳና እና ሙላቱ ማቲዮስንም ከልብ ማመስገን እሻለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ