ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ቅሬታ የሰበታ ከተማ ተጫዋቾች መደበኛ ልምምዳቸውን ካቆሙ ዛሬ ሁለት ቀን ሆኗቸዋል፡፡
በአዲሱ መርሀ ግብር መሠረት ታኅሣሥ 3 ረፋድ 4:00 ላይ በመክፈቻ ጨዋታ ድሬዳዋን ከተማን በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚገጥሙት ሰበታ ከተማዎች ወርሀዊ የደመወዝ እና የተገባላቸው ጥቅም በወቅቱ ስላልተፈፀመላቸው ልምምድ ማቆማቸውን የክለቡ ተጫዋቾች ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል። “በተደጋጋሚ ደመወዝ እንዲከፈለን ጠይቀናል። በተጨማሪም የተገባልን ቃል አልተፈፀመልንም። ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ ደመወዛችን ካልተከፈለ እና የተገባልን ጥቅም ካልተፈፀመልን ብለን ከትናንት ጀምሮ ልምምድ አቁመናል።” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
የተጫዋቾቹን ቅሬታ ተከትሎ ከክለቡ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ይሁንና ዛሬ ረፋድ የክለቡ የበላይ አካላት ተጫዋቾችን ሰብስበው “ወደ ልምምድ ተመለሱ፤ እየሰራችሁ ክፍያችሁን እንፈፅማለን” የሚል መልስ የሰጧቸው ሲሆን ተጫዋቾቹ ግን ተፈፃሚ ካልሆነ ወደ ልምምድ እንደማይመለሱ በመግለፅ ምላሽ እንደሰጡ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ