ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የ 2013 የውድድር ዘመን ነገ ይጀምራል። የዓመቱ የመክፈቻ የሆነው የሰበታ እና የድሬዳዋ ጨዋታን አስመልክተንም ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ዘግየት ብሎ ኅዳር 10 ላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረው ሰበታ ከተማ የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግም ነው ወደ ውድድሩ የሚገባው። በዚህም ከአሁኑ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋር ተለያይቶ የቀደሞውን የዋልያዎቹ አለቃ በመቅጠር የአሰልጣኝነት ለውጡን ተመጣጣኝ አድርጓል። በተጫዋቾች ዝውውር ረገድ በተሰረዘው የውድድር ዓመት የታየበትን ግብ የማስቆጠር ችግር ለመቅረፍ በሚመስል መልኩ ቡልቻ ሹራ፣ እስራኤል እሸቱ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ዱሬሳ ሹቢሳን አስፈርሟል። ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች በተዋቀረው የመሀል ክፍሉ ላይ ዳንኤል ኃይሉ እና ፉአድ ፈረጃን የጨመረ ቢሆንም በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴው ላይ ይበልጥ ጉልበት እና ፍጥነት ከመጨመር አንፃር በቦታው ላይ እንደታሰበው ተጨማሪ ዝውውሮችን አከናውኗል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ከዚህ በተጨማሪ የኋላ ክፍሉን ለማጠናከር ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎን እንዲሁም ተከላካዮቹ ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ ሙሉቀን ደሳለኝ እና መሳይ ጳውሎስን በእጁ አስገብቷል። ክለቡ ዛሬ ላይም ያሬድ ሀሰን ፣ አብዱልባሲጥ ከማል ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ዓለምአየሁ ሙለታን ዝውውር ማጠናቀቅ ችሏል።

ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር የተለያየው የሰበታ ከተማ የቡድን ስብስብ ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ባሳለፍነው ሳምንት ልምምድ አቁሞ የመመለሱ ጉሳይ ዘላቂ መፍትሄ ካላገኘ ከነገው የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ በፊት የሚኖረው የቡድን መንፈስ ላይ ተፅዕኖ እንዳያደርግበት ያሰጋል።

የአሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን ስብስብ የሆነው ድሬዳዋ ከተማ ከጥቅምት 19 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲያደርግ ሰንብቷል። ብርቱካናማዎቹ በስብስባቸው ውስጥ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ እና የመስመር አጥቂው ሲያን ሱልጣንን ከ20 ዓመት በታች ቡድናቸው ያሳደጉ ሲሆን የመሐል ተከላካዩ ሚኪያስ ካሣሁን ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከ20 ዓመት በታች ቡድን አስመጥተዋል። ቁልፍ ተጫዋቾቹን ሳይለቅ ለመቆየት የቻለው ድሬዳዋ በዝውውሩ ላይ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲተያይ የተመጠነ ተሳትፎ አድርጓል። ፊት መስመር ላይ በቋሚነት የግብ ምንጭ ሊሆን የሚችል ተጫዋች ለማስፈረም ያልሞከሩት ድሬዎች ዛሬ ሁለቱ ናሚቢያዊያን አጥቂዎች ጁኒያስ ናንጂቡ እና ኢታሙኑዋ ኬሙይኔን በማስፈረም የፊት መስመሩ ላይ አማራጮች ለማስፋት ሞክረዋል። በአንፃሩ ሀሚድ ጠፊቅን በግብጠባቂነት የቀድሞው ተጫዋቾቻቸው ዘነበ ከበደ እና ፍቃዱ ደነቀ እንዲሁም አራርሶ ጁነዲንን ለኋላ መስመራቸው አስፈርመዋል። ከዚህ በተጨማሪ አስጨናቂ ሉቃስ፣ ሙሉቀን አይዳኝ፣ ሱራፌል ጌታቸው እና ዳንኤል ደምሱ ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ አዲስ ፈራሚ አማካዮች ሆነዋል።

በነገው ጨዋታ ሰበታ ከተማ ያለምንም የጉዳት ዜና ወደ ለጨዋታው የሚቀርብ ይሆናል። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ግን ያሬድ ዘውድነህ እና ረመዳን ናስር በጉዳት ቡድናቸውን የማያገለግሉ ሲሆን የሙኸዲን ሙሳ መድረስም አጠራጣሪ ሆኗል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በ6 አጋጣሚዎች ተገናኝተው ድሬዳዋ በሜዳው ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሰበታ በሜዳው ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች በድል ተወጥቷል፡፡

– በስድስቱ ግንኙነታቸው ድሬዳዋ 4 ጎሎች ሲያስቆጥር ሰበታ 5 ጎሎችን አስቆጥሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ