የጅማ አባ ጅፋር የፈተና ጉዞ በምን ይቋጭ ይሆን?

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው የ2010 ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ የተለያዩ ፈተናዎች እያጋጠሙት ይገኛል።

በ2010 በክለቡ ታሪክ ስኬታማ ዓመት በማሳለፍ የሊጉ ቻምፒዮን ከሆነ በኃላ የተለያዩ ፈተናዎች እያጋጠሙት የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ለ2013 የውድደር ዘመን ከሳምንታት ዝግጅት በኋላ ሐሙስ ቡድኑ አዲስ አበባ ገብቷል። ሆኖም ከቀድሞ ግብጠባቂው ዳንኤል አጄ ደሞዝ አለመክፈል ጋር ተያይዞ ፊፋ ጅማ አባ ጅፋርን ማገዱ ይታወሳል።

ክለቡ ከነገው የአዳማ ከተማ ጨዋታ አስቀድሞ አዳዲስ ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች ለማፀደቅ ወደ ፌዴሬሽኑ ቢያቀናም ክፍያውን ለመፈፀም በመዘግየት ይሁን ባለመክፈሉ ባልታወቀ ምክንያት ፌዴሬሽኑ የአዲስ ተጫዋቾቹን ውል እንደማያፀድቅለት እና በ2012 በተጫወቱ ነባር ተጫዋቾቹን ብቻ መጠቀም እንደሚችል እንደተነገረው ለማወቅ ችለናል።

በዚህ መሠረት ጅማ አባ ጅፋር ለነገው ጨዋታ አሰራ አምስት ተጫዋቾች ብቻ ሲኖሩት ከአስራ አምስቱ ውስጥ ምንም አይነት ግብጠባቂ እንደሌለ ሰምተናል። ይህም በውድድሩ ጅማሬ ላይ በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው የሚመራው ቡድን ላይ የተጋረጠ የመጀመርያ ፈተና ሆኗል። በቀጣይ ክፍያውን በፍጥነት በመፈፀም በተሟላ ሁኔታ ወደ ውድድሩ እንዲገባ ለማድረግ የክለቡ አመራሮች ጥረት እያደረጉ የሚገኙ ሲሆን ጥረታቸው ሰምሮ ለውጦች ሊኖሩና ምናልባትም ተፈጥሯዊ ግብ ጠባቂ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ