ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ፋሲል ከነማ

የነገ ሁለተኛ መርሐ ግብር የሆነውን የጊዮርጊስ እና ፋሲል ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ለሁለት የውድድር ዓመታት ከዋንጫ አሸናፊነት የራቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም ድልን በሚያልምበት የውድድር ዓመት በአዲሱ አሰልጣኙ እየተመራ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። አዲስ ከቀጠራቸው ጀርመናዊው አሰልጣኝ ኤርነስት ሚደንዶርፕ ጋር ከጅምሩ የተለየው ክለቡ ለምክትሉ ማሂር ዴቪድስ ኃላፊነቱን በመስጠት ለውድድሩ ቀርቧል። የነገው ጨዋታ ይህ የአሰልጣኞች መቀያየር ከጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ በዝግጅት ላይ የሚገኘው ቡድን ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንደሚኖረው በምን ዓይነት መልክ እንደሚቀጥልም የሚያመላክት ጭምር ሊሆን ይችላል። 85ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዝውውር መስኮቱ በሊጉ በየክለባቸው ቁልፍ የሆኑ ተጫዋቾችን ማምጣትም ችሏል። በዚህም መሰረት አዲስ ግደይ ፣ ከነዓን ማርክነህ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ዘንድሮ በፈረሰኞቹ መለያ የምንመለከታቸው ተጫዋቾች ናቸው። የአዳዲሶቹ ፈራሚዎች የጥራት ደረጃ ሲታይም ከቡድኑ ነባር ተጫዋቾች ጋር በተለይም ከወገብ በላይ ባሉት ቦታዎች ላይ የሚኖረው የመሰለፍ ዕድልን የማግኘት ፉክክር ተጠባቂ እንዲሆን የሚያደርግ ነው።

በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ተጫዋቾቻቸውን የጠሩት ፋሲል ከነማዎች ረዘም ላለ ጊዜ በዝግጅት ላይ ከቆዩ ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ። ከልምምድ ባለፈ ፋሲል ከነማ ምንም እንኳን ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር ውጪ ቢሆንም በፉክክር ጨዋታ ላይ ራሱን ለመገምገም ዕድል ማግኘቱ በሊጉ ጥሩ አጀማመር ለማድረግ እንደሚረዳው የሚገመት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተከታታይ ዓመታት ወጥ የሆነ ቡድን መገንባት የቻሉት አፄዎቹ ያስፈረሟቸው ተጫዋቾች አቅምም የቡድኑን የስብስብ ደረጃ ከፍ ከማድረግ አንፃር በበጎ ጎኑ የሚነሳላቸው ነጥብ ነው። ልምድ ያለው ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ የመስመር ተከላካዩ ሳሙኤል ዮሃንስ ፣ አማካዩ ይሁን እንዳሻው እንዲሁም አጥቂዎቹ በረከት ደስታ እና ፍቃዱ ዓለሙ ዘንድሮ በጎንደሩ ክለብ የምንመለከታቸው ተጫዋቾች ይሆናሉ።

በግብ ጠባቂዎች ላይ ባጠነጠነው የቡድን ዜና ቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽን በጉዳት ሲያጣ ሌላኛው የግብ ዘቡ ለዓለም ብርሀኑ ደግሞ ከረጅም ጊዜ በኋላ ለጨዋታ ዝግጁ ሆኖለታል። በፋሲል ከነማ በኩልም በተመሳሳይ ለጨዋታው እንደማይደርስ የተነገረው አዲሱ ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ነው።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ሰባት ጊዜ (ሁለት ፎርፌዎችን ጨምሮ) ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ጊዜ ሲያሸንፍ ፋሲል ከነማ 2 አሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። የፎርፌ ጎሎችን ጨምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 ሲያስቆጥር ፋሲል 9 ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ