በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ አዳማ ከተማ በታፈሰ ሰረካ እና አብዲሳ ጀማል ግቦች በመታገዝ ጅማ አባ ጅፋርን 4-1 መርታት ችሏል።
ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ፍላጎት እንዳላቸው በሚያሳይ ነገር ግን የተቆራረጡ ቅብብሎች የተበራከቱበት አይነት አጀማመር ነበረው። በንፅፅር በጥቂቱ ሻል ይሉ የነበሩት አዳማዎች ከግብ ጠባቂው ራቅ ይል የነበረው የጅማ ተከላካይ ክፍል ጀርባ ኳስ ለመጣል ይሞክሩ የነበረበት ሂደት በቶሎ ውጤት አስገኝቶላቸውል። በተመሳሳይ ሁኔታ ኳስ አግኝቶ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው የኋላሸት ፍቃዱ ላይ የጅማ ግብ ዘብ አቡበከር ኑሪ ከሳጥን ውጪ ወጥቶ ጥፋት በመስራቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። የተጫዋቾች እጥረት ያለባቸው አሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸውም ከድር ኸይረዲንን በማስወጣት የሜዳ ላይ ተጫዋች የሆነው ኢዳላሚን ናስርን በግብ ጠባቂነት ለመጠቀም ተገደዋል። በዚህ አጋጣሚ የተሰጠውን ቅጣት ምት በላይ አባይነህ መትቶት በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት ሙከራም የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ሆኗል።
ጅማ አባ ጅፋሮች የተጨዋች ሽግሽግ በማድረግ ንጋቱ ገብረሥላሴን ወደ ኃላ በመመለስ ብዙዓየሁ እንዳሻውን በብቸኛ አጥቂነት በመጠቀም ጨዋታውን ቀጥለዋል። የተጠበቀውን ያህል የበላይነት ማሳየት ያልቻሉት አዳማዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ ባልቻ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ከተመለሰበት ኳስ በኋላ ሌላ ጠንካራ የሚባል አጋጣሚ አልፈጠሩም። ይልቁኑም 22ኛው ደቂቃ ላይ በፊት አጥቂነት ጨዋታውን ጀምሮ በቀይ ካርዱ ምክንያት አማካይ የሆነው የጅማው አብርሀም ታምራት በግንባሩ ያደረገው ሙከራ በታሪክ ጌትነት አድኖበታል። ሆኖም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ መላኩ ወልዴ በበላይ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት አዳማዎች በታፈሰ ሰረካ አማካይነት አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። ጨዋታው እጅግ በተቀዛቀዘባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች አዳማዎች የግብ ዕድል የመፍጠር ጉጉት ቢታይባቸውም ተጋጣሚያቸውን ሳያስጨንቁ ጅማዎችም አልፎ አልፎ ከቆሙ ኳሶች ለመሞከር ጥረት እያደረጉ አጋማሹ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ክፍት የነበረበት እና ግቦች በርከት ብለው የተስተናገዱበት ነበር። 47ኛው ደቂቃ ላይ ብዙአየሁ ከሱራፌል ዐወል ተቀብሎ ባደረገው ሙከራ ወደ ግብ መድረስ የቻሉት ጅማዎች ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ እየተቸገሩ መምጣታቸው አልቀረም። በመስመር ተከላካዮቻቸው የማጥቃት ተሳትፎ የሜዳውን ስፋት በአግባቡ ሲጠቀሙ የነበሩት አዳማዎች 57ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ እዮብ ማቲያስ አሻግሮት በመላኩ ከተጨረፈ በኋላ ታፈሰ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ባደረጋት ግብ ልዩነቱም አስፍተዋል። አዳማዎች በመልሶ ማጥቃት አስፈሪነታቸው በጨመረበት ቀጣይ ጨዋታዎች ከየኋላሸት የተነሱ ሁለት ጥሩ ዕድሎች በፀጋዬ ባልቻ እና በቃሉ ገነነ ተሞክረው በግብ ጠባቂው ድነዋል።
የጨዋታው የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ሦስት ግቦች የተቆጠሩባቸው ነበሩ። በአዳማዎች በኩል 80ኛው ደቂቃ ላይ ከበቃሉ በተላከ እና ተቀይሮ የገባው ፍሰሀ ቶማስ ሞክሮት በግብ ጠባቂው የተመለሰን ኳስ በሌላኛው ተቀያሪ አብዲሳ ጀማል ወደ ግብነት ተቀይሯል። በእዮብ እና በቃሉ ተጨማሪ የርቀት ሙከራ ያደረጉት አዳማዎች ጭማሪ ደቂቃ ላይ በድጋሚ ከእዮብ ማቲያስ የተሻማውን ኳስ አብዲሳ ጀማል በግንባሩ ገጭቶ መሪነትታቸው ወደ አራት አድርሶታል። ጅማ አባ ጅፋርን በባዶ ከመውጣት ያዳነችውን ግብ 84ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ደረሰ ከሮባ ወርቁ ተቀብሎ የጎል ክልሉን ለቆ በወጣው ታሪክ ጌትነት አናት ላይ በመላክ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ጨዋታውም በአዳማ 4-1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ አዳማ ጅማ አባ ጅፋር ሊጉን ከተቀላቀለበት 2010 የውድድር ዓመት ጀምሮ ከአራት የሊግ ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጅማን መርታት ችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ