” ሁላችንም እዚህ የመጣነው ከወልቂጤ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ነው ” ረመዳን የሱፍ

ወልቂጤን ከተማን በተቀላቀለበት ዓመት አጀማመሩ ያሳመረው እና ከኢትዮጵያ ቡና ከመመራት ተነስተው ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ ካስቻለው ረመዳን የሱፍ ጋር የተደረገ ቆይታ።

በፈጣንነቱ እና በታታሪነቱ ይታወቃል። በቦታው ከመከላከሉ ባሻገር በማጥቃቱም በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተመለከትነው እንገኛለን። የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እና ከዚህ ቀድም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታዳጊ ቡድን አድጎ ንግድ ባንክ በመፍረሱ ምክንያት ክለብ አልባ ሆኖ ለአንድ ዓመት ቆይታ ካደረገ በኃላ በትውልድ ስፍራው አሶሳ በአንደኛ ሊግ ከተጫወተ በኃላ በስሑል ሽረ ቆይታ በማድረግ ዘንድሮ ወልቂጤ ከተማን ተቀላቅሏል።

በቤቲ ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርቶ በወጣበት ጨዋታ በግሉ ጥሩ እንቅስቃሴ ከማድረጉ ባሻገር ከራሱ የሜዳ ክፍል ያስጀመረውን ኳስ ወደ ጎችነት በመቀየር የጨዋታው ኮከብ መሆኑን አሳይቷል። ይህን ተከትሎ ስለ ጨዋታው እና በቀጣይ ማድረግ ስለሞያስባቸው ጉዳዮች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቶናል።

” ይህ የዛሬው ጎል በፕሪምየር ሊግ ሁለተኛዬ ነው። ዓምና ሽረ እያለው ሶዶ ስታዲየም በወላይታ ድቻ ላይ ጎል አስቆጥሬ አውቃለው። በወልቂጤ ማልያ ግን የመጀመርያ ጎሌ ነው። ጨዋታው አሪፍ ነበር። ቡድናችን ገና አዳዲስ ተጫዋቾች ከነባር ተጫዋቾች ጋር የመቀናጀት ሥራ ስላልሰራን ገና አልተግባባንም። የመወሐድ ችግር እንዳለብን ዛሬ ሜዳ ላይ ታይቷል። ይህን ደግሞ በቀጣይ አስተካክለን እንቀርባለን። ከጊዜ ወደ ጊዜ በራሴ ላይ መሻሻሎች እና ለውጥን እያየሁ ነው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ መጫወቴ ደግሞ የበለጠ በራስ መተማመኔን እና አቅሜን እንዳወጣ አግዞኛል። በዛሬው ጨዋታም ጥሩ እንደነበርኩ አስባለሁ። ቡድናችን የበለጠ እየተዋህደ ሲመጣ ደግሞ የተሻለ እንቀሳቀሳለን። ዘንድሮ ከወልቂጤ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ነው ሁላችንም እዚህ የመጣነው። የቡድኑ ተጫዋቾች ተነሳሽነት በጣም ነው ደስ የሚለው። በየቦታው የሚጫወቱ ጥሩ ስብስብ አለን። ስለዚህ በቀጣይ የተሻለ ደረጃ ይዘን ለመጨረስ እንሠራለን።”

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ስለረመዳን ናስር ብቃት ይሄን ተናግረው ነበር።

“ጎል ማስቆጠሩ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ጎል የሚሆን ዕድል ፈጥሮ ነበር፡፡ ኢነርጄቲክ ነው ፤ በማጥቃትም በመከላከልም ጥሩ እና ንቁ ነበር፡፡ እኛም በጨዋታው ላይ በመስመር በኩል ለመጠቀም አስበን ነው የገባነው፡፡ ያሰብነውም ስኬታማ ነበር፡፡ ይህንን በቀጣይ ጨዋታዎችም መደጋገም ነው የሚጠበቅብን፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ