“የዛሬዋ ዕለት ለእኔ የተለየች ናት” – እዮብ ማቲዮስ

አዳማ ከተማ በጅማ አባጅፋር ላይ የበላይነት ወስዶ ለማሸነፉ ትልቁን ሚና ከተወጡ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደም ከሆነው ተስፈኛው ወጣት እዮብ ማትዮስ ጋር ቆይታ አድርገናል።

በአዳማ የታዳጊ ቡድን አንስቶ መጫወት የጀመረው እዮብ በ2010 ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ቢችልም የመሰለፍ እድል በማጣት ወደ ተስፋው ቡድን እየተመላለሰ ተጫውቷል። ከ2011 ጀምሮ በዋናው ቡድን ምንም ጨዋታ ሳይጫወት የቆየው እዮብ በትዕግስት ጠብቆ ለዓመታት ይመኝ ነበረውን የመጫወት ዕድል ዛሬ አግኝቷል። በአሰልጣኝ አስቻለው እምነት የተጣለበት ይህ ታዳጊ ለመጀመርያ ጊዜ የሊግ ጨዋታውን አድርጎ ጥሩ በመንቀሳቀስ ለሁለት ጎሎች መቆጠር ጉልህ ድርሻ አበርክቷል። የዛሬውንም እንቅስቃሴ በቀጣይ መድገም ከቻለ ወደ ፊት ትልቅ ተጫዋች መሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል። በዚህ ዙርያ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ከተጫዋች እዮብ ማትዮስ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።

“የዛሬዋ ቀን ለእኔ የተለየች ቀን ናት። ምክንያቱም እዚህች ቀን ለመድረስ ብዙ ጊዜ በትዕግስት ጠብቄያለው። እንደሚታወቀው አዳማ ትልቅ ቡድን ነው። ትልልቅ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች አሉ። እነርሱ እያሉ እኔ እድል ማግኘት ከባድ ነበር። ዛሬ ግን አሰልጣኞቼ አምነውብኝ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጫወት በመቻሌ በቃላት የማይገለፅ ደስታ ተሰምቶኛል። በምችለው አቅም መጫወት ችያለው። ለሁለት ጎሎች መቆጠር አስተዋፆኦ አድርጌያለሁ። ወደፊት ብሩህ ነገር ይታየኛል። ራሴን በትልቅ ደረጃ በማውጣት እስከ ብሔራዊ ቡድን መጫወት አስባለሁ። ለዚህ እንድደርስ ላደረገኝ ፈጣሪ ምስጋና አቀርባለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ