ወልቂጤ ከተማ ይግባኝ ጠይቋል

ከቀናት በፊት በጅማ አባጅፋር ተጫዋቾች ተገቢነት ላይ ክስ ያቀረቡት ወልቂጤ ከተማዎች ክሳቸው ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ይግባኝ ብለዋል።

ወልቂጤ ከተማዎች በሁለተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ አባጅፋርን ገጥመው ያለጎል ነጥብ ተጋርተው እንደነበር ይታወሳል። ከጨዋታው በኋላ በተጋጣሚያቸው ተጫዋቾች ላይ የተገቢነት ክስ ያቀረቡት ወልቂጤዎች ለክሳቸው “ተገቢ ምላሽ አላገኘንም” በሚል በድጋሚ ይግባኝ ብለዋል።

ክለቡ በትናንትናው ዕለት ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በፃፈው የይግባኝ ደብዳቤ “ጅማ አባጅፋር በዓለማቀፉ የእግርኳስ ማኅበር (FIFA) የሀገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ዝውውሮቸን እንዳይፈፅም እገዳ ተጥሎበት የነበረ እና የዝውውር መስኮቱ እስከተዘጋበት ታኅሣሥ 5 ድረስ የተጫዋቾ ደሞዝ ያልከፈለ በመሆኑ ዝውውር ማድረግ አይችልም ብሏል። በመሆኑም ክለቡ የመሠረተውን የተጫዋቾች ተገቢነት ክስ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ማየት ሲገባው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ባልተሰጠው ክስን የማየት ስልጣን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማብራሪያ ብቻ በመጠየቅ ላቀረብነው ክስ ምላሽ የሰጠበት ሒደት አግባብነት የሌነው እና ህገ ወጥ ነው።” ብሏል።

በይግባኝ ደብዳቤው ላይ እንደተቀመጠው ከሆነ ወልቂጤዎች ያቀረቡት ክስ ታይቶ በጨዋታው ፎርፌ እንዲሰጣቸው አለበለዚያም እስከ ዓለማቀፉ የእግርኳስ ገላጋይ ፍርድ ቤት (CAS) ድረስ እንደሚሄዱ ገልፀዋል።

ያስገቡት የይግባኝ ደብዳቤ 👇


© ሶከር ኢትዮጵያ