በባህር ዳር ከተማ እና ሲዳማ ቡና መካከል የተደረገው የአንደኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመዝጊያ ጨዋታ መገባደድ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ
ስለ ጨዋታው…
እንደ መጀመሪያ ቀን ጨዋታው መጥፎ አልነበረም። ብልጫ የወሰድንባቸውን ነገሮች 90 ደቂቃ ሙሉ ይዘን መዝለቅ አልቻልንም። ወጣ ገባ ነገሮች ነበሩ። ይህንን ነገርም ማስተካከል ይጠበቅብናል። ምንም እንኳን ጨዋታውን ብናሸንፍም በኳስ ስርጭት ላይ ብዙ ስህተቶች ነበሩብን። በተጋጣሚያችን በኩል ከመስመር የሚነሱትን ኳሶች ተቆጣጥረን የራሳችንን ጨዋታ ለመጫወት ነበር ያሰብነው። ይህን ተሳክቶልናል። በአጠቃላይ ግን ጨዋታውን በማሸነፋችን ደስ ብሎኛል።
ሁለት ግቦችን ስላስቆጠረው ፍፁም ዓለሙ…
ፍፁም ከዚህ የተሻለ መጫወት ይችላል። አቅም ያለው ተጫዋች ነው። በዛሬው ጨዋታም እስከ ጉዳቱ ነው የተጫወተው። ልዩነት ፈጣሪ የሆነ ተጫዋች ስለሆነ ግን አስገብተነዋል። ከእርሱም የምንፈልገውን አግኝተናል። ፍፁም ከተጎዳ በኋላም ቀይሬ ያስገባሁት ሄኖክ የመጨረሻውን ጎል ለባዬ አዘጋጅቷል። ስለዚህ ፍፁምንም ቀይሮ የገባው ጥሩ ነበር። በአጠቃላይ ዛሬ ተሳክቶልናል። ግን ቀድሜ እንዳልኩት ስህተቶቻችንን ማረም አለብን።
ስለ ፍፁም ጉዳት…
ስለዚህ ጉዳይ አሁን ላይ ለመናገር ይቸግረኛል። ከጨዋታው በፊት ልምምድ ላይ የነበረበት ጉዳት ይሁን ወይስ አዲስ ጉዳት የደረሰበት የሚለውን መረጃ ስለሌለኝ ምንም አልልም። ግን አመቱን ሙሉ እንዲያገለግለን ስለምንፈልግ በቀጣይ ማሳረፍም ካለብን እናሳርፈዋለን። ግን እንደ ጉዳቱ ይወሰናል።
ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ስለ ጨዋታው…
ዛሬ ጥሩ አልነበርንም። በተለይ ባህር ዳሮች የመከላከል ወረዳ አካባቢ ስንደርስ ኳሳችን ይበላሽ ነበር። ደግሞም የምናበላሻቸው ኳሶች ናቸው በተደጋጋሚ ወደ እኛ ሲመጡ የነበረው። ጥቃቅን ስህተቶችን እንሰራ ነበር። ተከላካይ ፣ አማካይ እና አጥቂ ክፍላችን ጥሩ አልነበረም። በአጠቃላይ እንደ ቡድን ጥሩ አልነበርንም። ይህ ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታ ነው። ብዙ ነገሮችን አስተምሮናል። በቀጣይ በታክቲክም ሆነ በአጨዋወት የተሻለ ነገር ይዘን ለመምጣት እንሞክራለን።
ስለ አዲስ ግደይ ቡድኑን መልቀቅ እና ተፅዕኖው…
ዛሬ ይህ ነው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም 6 እና 7 ተጫዋቾቻችን በተለያዩ ምክንያቶች አልተጫወቱም። በቀጣይ ግን ይደርሳሉ ብዬ አስባለሁ። በአዲስ ምትክም የመጣ ተጫዋች አለ። እርሱም በተመሳሳይ በጉዳት አልተጫወተም። በጨዋታው ግን ተፅዕኖ የፈጠረብን እኛ ስንለማመድበት የነበረው የሰው ሰራሽ ሜዳ እና ዛሬ የተጫወትንበት የተፈጥሮ ሜዳ መለያየቱ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የአየር ሁኔታውም ትንሽ ተጫዋቾቹን ከብዷቸው ነበር። ለዛም ነው አጥቅተን በቶሎ መመለስ ያልቻልነው። ከዚህ በኋላ ግን ቆይታችን እዚሁ ስለሆነ ሁለቱን ነገር እንለምዳለን ብዬ አስባለሁ። ቡድናችን ግን በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ መሠረት ያደረገ ቡድን አደለም። የእርሱም መኖር እና አለመኖር አደለም ክፍተታችን።
ስለ ቡድኑ ብዙ ግብ ማስተናገድ…
የመጀመሪያው ጎል የገባብን በመሐል ተከላካዮቻችን አለመግባባት ነው። ሁለተኛውም የባህር ዳር አጥቂ ከመሐል ተከላካያችን ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ አቅሙን በመጨረሱ እና በመውደቁ በቀላሉ የገባብን ነው። ሦስተኛውም በተመሳሳይ የተቆጠረ ግብ ነው። ቀድሜ እንዳልኩት የሚበላሹብንን ኳሶች ነው ባህር ዳሮች ይዘው እየመጡ አደጋ የፈጠሩብን። ዞሮ ዞሮ ግን የቡድናችንን ደካማ ጎን ስላየን በቀጣይ አርመን እንመጣለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ