የቀድሞ የአዳማ ተጫዋቾች ቅሬታቸውን ገለፁ

በአዳማ ከተማ እስከተሰረዘው የውድድር ዓመት ሲጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች የደመወዝ ጥያቄችን ሊመለስ ባለመቻሉ ጉዳዩን ወደ ካፍ ልንወስድ ነው ብለዋል፡፡

በ2011 በክለቡ ሲጫወቱ ለነበሩ ተጫዋቾች የሁለት ወራት ደመወዝ እና እንዲሁም በተሰረዘው የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በክለቡ ይጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች የሰባት ወራት ደመወዝ እስካሁን እንዳልተከፈላቸው ገልፀው ክለቡ አምና ለተጫዋቾቹ የሦስት ወራት ደመወዝ ብቻን ከተስማሙበት የውል ክፍያ ውጪ የከፈላቸው ቢሆንም እሱም አግባብ እንዳልሆነ እና ደመወዛቸው በሙሉ በተስማማንበት ውል እንዲከፈለን በማለት ከወራቶች በፊት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቅሬታ ደብዳቤን በመያዝ ፌድሬሽኑ ተፈፃሚ ያድርግልን ብለው ክሳቸውን ማስገባታቸው ይታወሳል፡፡ ይህን ጉዳይ ተመልክቶ የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ክለቡ እንዲከፍል በተደጋጋሚ በደብዳቤ ልኮ ይክፈላቸው ቢልም ክለቡ ምንም አይነት መልስ ለተጫዋቾቹ ባለመስጠቱ በመጨረሻም የእግድ ውሳኔን አስተላልፎበት እንደነበረም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡

ይሁንና ፌድሬሽኑ ክለቡ ላይ የእግድ ውሳኔ ቢያስተላልፍም “ክለቡ ግን ደመወዛችንን ሳይከፍል በምን አግባብ ተጫዋቾችን አስፈርሞ ወደ ውድድር ገባ? ይህ በፌዴሬሽኑ ውስጥ የተበላሸ አሰራር እንዳለ ያሳያል። ከአሁን በኋላ ፌድሬሽኑ ለእኛ ጥብቅና እንደማይቆም አረጋግጠናል። ስለዚህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የእኛን ጉዳይ ቸል ብሎ ለክለቡ በመወገኑ እንዲሁም አዳማ ከተማ ደግሞ በገባው ውል መሠረት ደመወዛችንን ስላልፈፀመ ጉዳያችንን ወደ ካፍ ይዘን ልንሄድ ተዘጋጅተናል፡፡” ሲሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ጉዳዩን አብራርተዋል፡፡ ቅሬታ አቅራቢ ተጫዋቾቹ አክለውም ከሰሞኑ አዲስ አበባ ከተሰባሰቡ በኃላ በጉዳዩ ተወያይተው ወደ ካፍ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እንደሚያመሩ ነግረውናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ