ስለ ሳዳት ጀማል ሊያውቋቸው የሚገቡ ዕውነታዎች

በጠንካራ ግብጠባቂነቱ የሚታወቀው በሀገሪቱ ትልልቅ ክለቦች እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ ለረጅም ዓመት ማገልገል የቻለው የቀድሞ ድንቅ ግብጠባቂ ሳዳት ጀማል ማነው?

በኢትዮጵያ የግብጠባቂዎች አብዮት በተነሳበት ዘመን ከተገኙ ኮከብ ግብጠባቂዎች መካከል አንዱ ነው። በስልጤ ዞን ተወልዶ እስከ አምስት ዓመቱ ድረስ ይደግ እንጂ የዕድሜውን አብዛኛውን ዘመን የኖረው በአዲስ አበባ ተክለሃይማኖት ጡረታ ሠፈር በምትባል አካባቢ ነው። አባቱ ለእግርኳስ ካላቸው ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ አለ ከተባለ የማይቀሩ ቀንደኛ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ናቸው። ሁሌም ታዲያ በአንድ እጃቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ አርማ በሌላ እጃቸው አንድ ልጃቸውን ይዘው ወደ ስታዲየም ይመጡ ነበር። ሁሌም ስታዲየም መጥቶ በሚመለከተው ጨዋታ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ፣ በለጠ ወዳጆ፣ አብዱ ሳላህ (ፈቱሼ)፣ ፀጋዘአብ አስገዶም እና ሌሎችንም እየተመለከተ ግብጠባቂ የመሆን ፍላጎቱ እየጨመረ መጥቷል።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ቁመና እና ቅልጥፍናውን አይተው የስፖርት መምህሩ አንተ ግብጠባቂ መሆን አለብህ በማለት በእርሳቸው ምርጫ ግብጠባቂነትን በትምህርት ቤት ውድድር ጀምሯል። የሳዳት ጀማል አቅም፣ አጀማመሩን እና የነበረውን እድገት የተመለከቱ ሁሉ በክለብ ታቅፎ ራሱን እያሳየ ማደግ አለበት በሚል በወቅቱ በአሰልጣኝ ቢረጋ ወደሚሰለጥነው መብራት ኃይል “ሲ” ቡድን ከብዙ ታዳጊዎች መሀል አልፎ በ1985 መቀላቀል ቻለ። ወደ ዋናው ቡድን እስካደገበት 1989 ድረስ ለአራት ዓመታት በመብራት ኃይል ቆይታ ቢያደርግም በለጠ ወዳጆ እና ፀጋዘአብ አስገዶምን ሰብሮ በመጀመርያ አሰላለፍ መግባት የማይታሰብ መሆኑን በመረዳት በ1990 ለወራት ያህል ሊጫወት ወደ ደብረ ብርሀን ብርድ ልብስ አምርቶ ቆይታ አድርጓል። በመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ በመመለስ ጥሩ ቆይታ አድርጓል። በአንድ ወቅት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከቀድሞ የፊፋ ፕሬዝደንት ሴፕ ብላተር ጋር በጃን ሜዳ ጉብኝት እያደረጉ ሳዳት ጀማል ሲጫወት ተመልክተውት በጊዜው ሌሎች በትልልቅ ክለቦች የሚጫወቱ ግብጠባቂዎች ቢኖሩም “መብራት ኃይል ነኝ ጊዮርጊስ ነኝ አይሰራም። ዋናው ብቃት ነው” በማለት ከታችኛው የዲቪዚዮን ውድድር ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ለመረጥ ችሏል።

ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን መመረጡ የበለጠ ራሱን ለማሳየት ረድቶት እንዲሁም በየጊዜው ዕድገቱ እና አቅሙ እየጨመረ በመምጣቱ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ቀጥሎ ወደ ኒያላ በማቅናት ኒያላ ከታችኛው ዲቪዚዮን አንስቶ ፕሪምየር ሊግ እስከገባበት ጊዜ ድረስ በነበረው ሒደት ከሌሎቹ ተጫዋቾች ጋር በመሆን የእርሱ አስተዋፆኦ ከፍተኛ ነበር። ለዚህም ይመስላል ወደ አርጀንቲና የወጣቶች ዓለም ዋንጫ አይሂድ እንጂ ቡድኑ በኢትዮጵያ በተስተናገደው የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ደቡብ አፍሪካን አሸንፎ የዓለም ዋንጫ እስከገባበበት ጊዜ ድረስ የወጣት ቡድኑ ቋሚ ግብጠባቂ በመሆን ማገልገል ችሎ የነበረው። በመጨረሻ ከአሰልጣኝ ዲዬጎ ጋርዚያቶ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከብሔራዊ ቡድኑ ውጭ ቢሆንም።

በክለብም በብሔራዊ ቡድንም አብሮት የተጫወተው የቀድሞ ድንቅ አጥቂ ማሞዓለም ሻንቆ (አስፕሬላ) ስለ ሳዳት ሲናገር “ሳዳት ከታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ጀምሮ አብሮኝ የተጫወተ ጓደኛዬ ነው። በጣም የማደንቀው ግብጠባቂ ነው። በፀባዩም ምንም ነገር የማይመስለው፣ ዴንታ የሌለው፣ የማይጨነቅ ግብጠባቂ ነው። በጣም ቀልደኛ የሆነ የሚያስቅ ጓደኛዬ ነው። እኔ ስለ እርሱ መናገር ይከብደኛል። በጣም ጎበዝ የማደንቀው፣ የማከብረው ግብጠባቂ በተለይ ከእኔ ጋር ብዙ ነገሮችን አብሮ ያሳለፈ ጥሩ ወንድሜ ነው።” ብሎታል።

የአራት ዓመት ስኬታማ ቆይታውን በኒያላ አጠናቆ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወደሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በማምራት አይረሴ አጋጣሚዎችን በማሳለፍ ጥሩ ቆይታ አድርጓል። ሳዳት በቡና ቤት በቆየባቸው ሁለት ዓመታት በጣም ጥሩ ብቃቱ እንዳለ ሆኖ ፈገግ የሚያሰኙ ከስፖርት ቤተሰቡ አዕምሮ የማይጠፉ ብዙ ገጠመኞችን አሳልፏል። ምንም እንኳን በተጫወተባቸው ክለቦች አጫጭር ቆይታ ቢኖረው በአመዛኙ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ይገባ እንደነበረ መመልከቱ በወቅቱ የነበረውን ብቃት ማሳያ ነው። ከቡና በመቀጠል መከላከያ፣ ሙገር እና ሀዋሳ ከተማ ከተጫወተ በኃላ በ2002 ጓንቱን ለመስቀል ችሏል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ1990 ለታዳጊ ቡድን ከተመረጠበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም የዕድሜ እርከን ሀገሩን ያገለገለው ሳዳት በ1997 በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተካሄደውና ብሔራዊ ቡድኑ ዋንጫውን ባስቀረው የሴካፋ ዋንጫ ድል ውስጥ የቡድኑ አባል ነበር።

በኢትዮጵያ ቡና አብሮት የተጫወተው የቀድሞ ድንቅ ተከላካይ አንዳርጋቸው ሰለሞን ስለ ሳዳት ጀማል ሲናገር “አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ለራሱ ለሚከተለው አጨዋወት ይመቸኛል ብሎት ነው ቡና ያመጣው። በዚህ ዘመን ግብጠባቂዎች ኳስን መጫወት አለበት ከመባሉ በፊት በዛን ዘመን ኳስን መስርቶ በእግሩ ይጫወት የነበረ ግብጠባቂ ነው። ለእኛ ለተከላካዮች ምቾት እንዲሰማን የሚያደርግ ቀለል አድርጎ የሚጫወት በረኛ ነው። ግብጠባቂ ብቻ ነው የማትለው ሁሉን ነገር አቅፎ የያዘ ድንቅ ግብጠባቂ ነበር። ስለ እርሱ ብዙ መናገር ይቻል ነበር። ሆኖም መጫወት እየቻለ በጊዜ ነው ያቆመው። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከታዩ ድንቅ ግብጠባቂዎች አንዱ ነበር።” በማለት ምስክርነቱን ይሰጣል።

ጓንቱን ከሰቀለ በኋላ ወደ ግብጠባቂ አሰልጣኝነቱ በመግባት ሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ አዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ቡድንን በማሰልጠን በረጅም ዓመት ያገኘውን ከፍተኛ ልምድ ሲያካፍል ቆይቶ በአሁኑ ወቅት በትውልድ ሥፍራው ወራቤ ከተማ ከአንጋፋው አሰልጣኝ ጋሽ ከማል ጋር በመሆን የታዳጊዎች ፕሮጀክት በመክፈት ትኩረቱን ታዳጊዎች ላይ በማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራ ይገኛል። ከ25 ዓመት በላይ በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት ያሳለፈው ይህ የቀድሞ የዘጠናዎቹ ድንቅ በግብጠባቂ ሳዳት የዛሬው እንግዳችን በመሆን የእግርኳስ ህይወቱን እንዲህ አጫውቶናል። መልካም ንባብ!

“ከምንም በላይ ለኔ ስኬቴ የምለው እና የማልረሳው ወደ አርጄንቲና በሄደው ወጣት ቡድን ውስጥ ባልካተትም መላ ኢትዮጵያን ባነቃነቀው የአፍሪካ የወጣቶች ዋንጫን ደቡብ አፍሪካን አራት ለአንድ ያሸነፍንበት ድል በታሪክ እስካሁን ድረስ እንዲህ ያለው ውጤት ድልም እንደ ሀገር አልታየም። የነበረው ደስታ የህዝቡ ስሜት እስከ ህይወቴ መጨረሻ ድረስ የምረሳው አይደለም። ፈጣሪ አስክቶልኛል የምለው ለሀገሬ አንድ ነገር ሰርቻለው የምለው ትልቁ ድል እና ስኬቴ የምለው ይሄ ነው። በመቀጠል አዲስ አበባ በተዘጋጀው የሴካፋ አላሙዲን ሲንየር ቻሌንጅ ዋንጫ ያነሳንበት ለኔ ሌላው ስኬት ነበር። እንዲሁም ቡና መጫወቴ ለኔ ከምንም በላይ የምደሰትበት በቡና በነበረኝ ቆይታ አንድም ቀን ተጠባባቂ ሳልሆን ሙሉውን እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ የተጫወትኩበት እና ትልቅ ስም ያገኘሁበት በመሆኑ ለኔ ትልቅ ስኬት ነው። በመጨረሻም አባቴ ከልጅነቴ ጀምሮ ስታዲየም ይዞኝ ይሄድ ነበር። እኔ ደግሞ ስጫወት ቁጭ ብሎ ለማየት መታደሉ ሌላው ትልቁ ስኬቴ ነው። በአጠቃላይ ያገኘኋቸው ስኬቶች ሀገሬን እንድወድ፣ ያገኘሁኝ ያህል እንዲሰማኝ ያደረገኝ ትልቁ ስኬቴ እግርኳሱ ነው። በአጠቃላይ በጣም በሁሉም ነገር ደስተኛ ነበርኩ።

“በህይወቴ የምቆጭበት ነገር የለም። በኳስ ጨዋታ ጠግቤያለሁ። በሁሉም በተጫወትኩበት ክለብ ተቀምጬ አላውቅም። በሆነ ክለብ ባልጫወት ቁጭ ብል ኖሮ ይቆጨኝ ነበር። በሄድኩበት ክለብ ሁሉ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አላንሳ እንጂ በሁሉም ክለብ ከሀዋሳ ከተማ ውጭ በዋንጫ የታጀበ ጊዜን ነው ያሳለፍኩት፤ በዚህም ስኬታማ ነኝ። ሆኖም በ1996 ኢትዮጵያ ቡና በምጫወትበት ዘመን ከጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት የተሳሳትኳት ኳስ እና ኢትዮጵያ ቡና ሻምፒዮን መሆን የሚችልበትን ዕድል እኔም ኮከብ ተጫዋች የምሆንበትን ዕድል ያጣሁበት አጋጣሚ ሁሌም የምቆጨበት ጊዜ ነው።

“በ1996 የተፈጠረው ከጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት ያንን ጨዋታ ብናሸንፍ ኖሮ ሻምፒዮን መሆናችንን የምናረጋግጠበት ነበር። በወቅቱ ሁለት ለአንድ እየመራን ባለንበት ሁኔታ ኳስ ይዤ ባጋጣሚ ተፈንክቼ ደሜ እየፈሰሰ ጭንቅላቴን ተጠቅልዬ ነበር። የያዝኩትን ኳስ ለእኛ ልጅ እሰጣለው ብዬ ኳሱ ተጠቅልሎ መሐል ላይ ያለው ሙሉዓለም ረጋሳ አገኘው መሰለኝ ከጎልም ውጭ ነበርኩ፤ ያ ኳስ ጎል ገብቶ ቡና ዋንጫ ያጣበት እኔም ዓመቱን ሙሉ የለፋሁት ኮከብ ተጫዋች የመሆን እድሌን ያሳጣኝ መጥፎ አጋጣሚ ነው።

“ኒያላ… እውነት ለመናገር አንድን ቡድን የሚገነባውም የሚያፈርሰውም የክለቡ አስተዳደሮች ናቸው። በወቅቱ የነበሩ የኒያላ አስተዳደር እነ አቶ ምናሴ፣ አቶ በቀለ፣ አቶ ጌታቸው የሚባሉ እግርኳሱን የሚረዱ ስፖርት አዋቂ ሰዎች ነበሩ። በኃላ ነው የማይሆኑ አመራሮች ከመጡ በኃላ ነው ቡድኑ እየተበላሸ የመጣው። በእውነት የአስተዳደር ችግር እንጂ መፍረስ የሌለበት ቡድን ነው። በኢትዮጵያ እግርኳስ ትልቅ ውለታ ያበረከተ፣ እኛን በጥሩ ፍቅር ትልቅ ተጫዋች ያደረገን፣ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን ያበቃ፣ እስከ አሁኑ ታፈሰ ሰለሞን ድረስ ብዙ ታዳጊዎችን በሻንበል መላኩ አማካኝነት መፍጠር የቻለ፣ ብዙ ደጋፊዎች የነበሩት ይህ ቡድን በአንድ ሰው ምክንያት ኒያላ እንዲህ በመሆኑ በጣም ነው የምናዝነው።

“በታላቁ ክለብ ቡና የነበረኝ ቆይታ በጣም አስደሳች ነበር። በጣም በማከብረው አሰልጣኝ ካሳዬ ተፈልጌ ቡና እንድገባ ስጠየቅ ያለምንም የገንዘብ ድርድር ቡና ለመጫወት ከነበረኝ ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ በሙሉ ደስታ ልፈርም ችያለው። ምክንያቱም ቡና ትልቅ ቡድን ነው ይህን ማልያ መልበስ ስለምፈልግ እና ወደፊት ሁሌም በታሪክ የሚቀር ስለሆነ ለቡና ለመጫወት ወዲያውኑ ነው የፈረምኩት። በሁለት ዓመት ቆይታዬም ሽንፈት ያየሁት ከአራት ጨዋታ አይበልጥም። ትልቅ ስም ያገኘሁበት እና ትልቁን ብቃቴን ያሳየሁበት ቡድን ነው። ለኢትዮጵያ ቡና በመጫወቴም ትልቅ ክብር አለኝ። በቡና ቆይታዬ የዙሩን ዋንጫ ባናገኝም ሁለት የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማንሳት ችያለው።

“ያው እኔ ስጫወት ፉገራዎች ቀልዶች አሉ፤ ብዙ ገጠመኞች አሉ። በነገራችን ላይ ስጫወት ጎል ሲገባ አይገርመኝም ብናሸንፍም አይገርመኝም። ለኔ ምንም የሚያስደንቀኝ ነገር የለም። ዋናው ሥራዬን በተግባር ይዤ መውጣት ላይ ነው የማተኩረው። አንዳንዴ ጎል ሲገባ ሲናገሩህ የምትመልሰው መልስ አስቋቸው የሚሄዱ አሉ። አንዴ ምን ሆነ መሰለህ ጋሽ ፀጋዬ ደስታ የሚባሉ አሰልጣኝ አሉ። ሜዳ ላይ አንድ ጎል ገባብኝና ተቀየር ይሉኛል። እኔ ባላየ ባልፍም ውጣ ብለው ጨቀጨቁኝ። ዳኛው ‘ውጣ ተቀየር እያሉህ ነው’ ሲለኝ ‘አልወጣም ተዋቸው፤ አንተ ብቻ ጨዋታውን አጫውት አልኩት። እኔ በጎሉ መቆጠር ሒደት ላይ ምንም ያጠፋሁት ነገር የለም። የተሳሳተውን ተከላካዩን ትተው ያላጠፋሁትን ውጣ ሲሉኝ አልወጣም አልኳቸው። እረፍት ወጥተን መልበሻ ክፍል ስነገባ ጋሽ ፀጋዬ ‘እንዴት ይህ ጎል ይገባል?’ ሲለኝ ‘እንዴ ጎል የተሰራው ሊገባበት አይደለም?’ አልኩት። በዚህ ሰዓት እንዳለ የሳቁ በት ገጠመኝ አለ። ሌላው ከአስፕሪላ ጋር በጣም እንፎጋገር ነበር። እኔ እና እርሱ ካለን ሰርቪሱ በሳቅ ነው የሚሞላው። አንድ ጊዜ ከሱሉልታ ስንመጣ መኪና ውስጥ የሆነ ጥያቄ እና መልስ ሬዲዮ ላይ ይጠየቅ ነበር። በዓለም ላይ ትልቁ ጎሬላ የት ሀገር ነው የሚገኘው ሲል አሰፕሪላ ከፊቴ ቁጭ ብሎ ስለነበር ‘ይሄው ፊለፊት ተቀምጦ ነው ያለው’ ብዬ ስናገር ሰርቪሱ ውስጥ የነበሩት የሳቁት ሳቅ የማልረሳው ገጠመኝ ነው። የመጨረሻ… ቡና እያለሁ ከትራንስ ጋር ስንጫወት በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ትራንሶች የቅጣት ምት ያገኛሉ። አጋጣሚ ሆኖ ከዛ ርቀት ቦታ ወደ ጎል ይመታዋል ብዬ ስላላሰብኩ ጎሉን ለቅቄያለሁ። ተመልካቹ ግባ እያለኝ ነው እኔ ምንም አልሰማም። ልጁ ኳሱን በቀጥታ ወደ ጎል መቶት ባለቀ ሰዓት ጎል ይቆጠራል። የቡና ደጋፊ ከፍተኛ ተቃውሞ ያቀርባሉ። ወደ መልበሻ ክፍል ስገባ እኔ እየሳቅኩ ነው የምገባው ምንም አይመስለኝም። በኃላ ካሳዬ ‘ሰርቪሱን የጭነት መኪና ነው የምታደርገው። ልብስህን ለብሰህ ኮፍያ አድርገህ በጊዮርጊስ በር አድርገህ ውጣ’ አለኝ። እኔም በዛ አድርጌ ተሸፋፍኜ በጥቁር አንበሳ ዳገቱን በእግሬ እየወጣሁ ማንም ሰው ሳያየኝ ሄድኩ። መንገድ ላይ ሰው ይሳደባል፤ እኔን መሆኔን ግን አያውቅም። እየሰማሁ ቤት የደረስኩበት አጋጣሚ ትዝ ይለኛል። ይገርማል በሳምንቱ አዳማ ላይ ቡድኑን ይዤ ወጥቼ አንድ ለባዶ አሸንፈን ስንወጣ ደጋፊው እኔን ተሸክሞ ሲጨፍር ካሳዬ ‘በል ውረድ ነገ ደግሞ የሚሆነው አይታወቅም’ ያለኝ ጊዜ አረሳውም።

“አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ… እዚህ ሀገራችን በነበረው የአፍሪካ ወጣቶች ውድድር በሁሉም ጨዋታ ላይ ተሰልፌ ነበር። በኋላ ከአሰልጣኝ ጋርዚያቶ ጋር በነበረው አለመግባባት ወደ አርጀንቲና ሳልሄድ ቀርቻለሁ። ምክንያቱ በልምምድ ወቅት በሚሰጡ ስልጠናዎች ዙርያ ግምገማዎች ነበሩ። በዛን ሰዓት እኔ አሰልጣኝ ጋርዝያቶን የሚተች ነገር ተናገርኩ። ስልጠናዎቹ ከበድ የሚሉ ናቸው። ለምሳሌ ‘ግብጠባቂ ሆነን ያን ያህል ተራራ መዞሩ ለምን ያስፈልጋል?’ የሚል አንዳንድ ጥያቄዎች አንስቼለት ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአስተርጓሚ ችግር እንደሆነ አላውቅም በዚህ ንግግሬ ጠመደኝና ወደ አርጀንቲና በመሄድ እንዳልጫወት ተደረግኩ። እንግዲህ የተናገርኩትን መልዕክት በሚገባ ሳያደርሱት በመቅረታቸው ጠመደኝ እንጂ በዛን ወቅት በነበረኝ አቅም እና ችሎታ የሚደሰት ሰው ነበር። ‘እዚህ ሀገር መጫወት የለብህም’ በማለት ሁሌም ይነግረኝ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተመረጥኩበት ጊዜ ጀምሮ ግብጠባቂነትን እስካቆምኩበት ጊዜ ድረስ አንድም ቀን ሳላርፍ ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ መጫወት ችያለው። ከአሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ፣ ገዛኸኝ ማንያዘዋል፣ ጋሽ ከማል አህመድ፣ ፀጋዬ ደስታ፣ አብርሀም ተክለሃይማኖት፣ ጋሽ ሰውነት ቢሻው፣ ወንድማገኝ ከበደ፣ ሥዩም አባተ በአጠቃላይ ከሁሉም አሰልጣኞች ጋር ከውጭዎቹ አሰልጣኞች ከጋርዚያቶ፣ ኤፊ ኦኔራ ጋር ሳይቀር አብሬ ሰርቻለሁ። በዚህም በጣም ደሰረተኛ እና እድለኛ ነኝ።

“በአሰልጣኝነቱ አጀማመሬ ሀዋሳ እያለሁ ነው የጀመርኩት። በመቀጠል ሲዳማ ቡና ሰርቻለሁ። በ2008 ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕናን ማሰልጠን ችዬ ነበር። በተለያዩ ሥራዎች ምክንያት እስካቆምኩበት ጊዜ ድረስ በአሰልጣኝ መሠረት ማኒ ይመራ የነበረው አዲስ አበባ የሴቶች ቡድን መሥራት ችዬ ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰጡ የአሰልጣኝ ኮርሶችን ከ A ላይሰንስ በቀር ሁሉንም ስልጠናዎችን ወስጃለሁ። የግብጠባቂ አሰልጣኝነት ኮርስ ሳይቀር ወስጃለሁ። ብቃቱ አለኝ፤ ልምዱም ኖሮኝ እየሰራሁ ነበር። አሁን በወራቤ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ላይ እየሰራሁ ነው።

“አባቴ የቀለጠ የጊዮርጊስ ደጋፊ ነው። ከድሮም ጀምሮ በጊዮርጊስ የማይደራደር ክብር የሚሰጥ የታወቀ ደጋፊ ነው። ከእኛ ከቤተሰቡ በላይ ቤት ውስጥ ገጠር የሚሄድ ሬሳ ተቀምጦ፣ አቆዩት ብሎ ስታዲየም ገብቶ አስራ ሁለት ሰዓት ጨዋታ ጨርሶ በማታ አስከሬን ይዞ የሄደበትን ሁኔታ አስታውሳለሁ። ይሄን ያህል ለጊዮርጊስ ትልቅ ዋጋ የሚከፍል አባት ነው ያለኝ። በዚህ አጋጣሚ ለአባቴ የተለየ ክብር እንዳለኝ መግለፅ እፈልጋለሁ። እኔ የተሻለ ደረጃ እንድደርስ በመምከር፣ ሜዳ ውስጥ የማጠፋቸው ነገሮች ካሉ እንዳስተካክል እየነገረኝ ከአሰልጣኝ እኩል ብዙ ዋጋ የከፈለልኝ የተለያዩ ስኬቶችን እንዳሳካ ትልቅ ውለታ የወሰለልኝ ሰው ነው። በዚህ አጋጣሚ አባቴን በጣም አመሰግነዋለሁ።

“አባቴ የጊዮርጊስ ደጋፊ የነበረ በመሆኑ የ1996 የሰራሁትን ስህተት በማገናኘት የተለያዩ የተሳሳቱ በመላ ምት የሚወሩ ወሬዎች ይነገራሉ። ለአባቱ እንዲህ አድርጎ የሚባሉ ነገሮች ከሌላ ከጥቅማጥቅም ጋር አያይዘው የሚያወሩ አሉ። ለኔ ግን ከዛ ጥቅም በላይ፣ ከየትኛውም ሀብት በላይ የቡና ገብያ ክብር ነው ለእኔ የሚቀድመው። ከደጋፊው በፊት የምደሰተው እኔ ነኝ፣ ኮከብ ተጫዋች ክብርን ለማግኘት ስለፋ ስጥር ነበር። ዓመቱን ሙሉ ቡድኑን ስጠቅም ከርሜያለሁ። በወቅቱ የተባለው ነገር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። አባቴ እንዲያውም ደስ የሚለው እኔ ኮከብ ተጫዋች ሆኜ ብሸለም ነው እንጂ የጊዮርጊስ ማሸነፍ መሸነፍ አይደለም። በርግጥ በጊዮርጊስ አይደራደረደም ይታወቃል። ነገር ግን የኔን ኮከብነትን ያስቀድማል የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ አንግል ደጋፊዎችን ለማሳሳት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት በወቅቱ የኔ ስም ሲገን የማይወድ ሰው አሁን ስሙን መጥራት የማልፈልገው ሰው ነው ይሄን የሚያስወራው። የሚገርምህ አንተነህ አላምረው በዚሁ ዓመት ተባረረ። አንተነህ ቢኖር ኖሮ ዋንጫ እንወስድ ነበር። ሆኖም የራሱ ስም ብቻ እዛ ክለብ ውስጥ እንዲገን የሚፈልግ ሰው ነበር። ያው ይታወቃል ስሙን መጥራት ስለማልፈልግ ነው። ዋንጫውን ያጣነው አንተነህ አላምረው የወጣ ጊዜ ነው። ስለዚህ ከኔ ጋር አይያዝም። ሌላው በተከታታይ አምስት ጨዋታ ነጥብ እየጣልን ነው ከጊዮርጊስ ጋር መጨረሻ የተጫወትነው። ስለዚህ ከአምስቱ ጨዋታ አንዱን ለምን አላሸነፍንም። ከወንጂ፣ መተሀራ፣ አርባምንጭ እና ሙገር ሌሎች ተራ ተራ ቡድኖች ማሸነፍ አቅቶን ነው ዋንጫ ያጣነው። ከጊዮርጊስ ጋር ይሄ የተነሳው እኔ ከቡና ክብር በላይ የማስቀድመው ሌላ ጥቅም የለም። እኔ በዚሁ አጋጣሚ የቡና ደጋፊ በዚህ ልክ የተረዱ ካሉ ቢያስተካክሉ ጥሩ ነው። ለኔ ቡና ማለት ከየትኛውም ክለብ በላይ ትልቅ ክብር የሰጠኝ ደጋፊ በምንም ነገር የማገኘውን የኮከብነት ክብር የማበላሽ ሰው አይደለውም። እንደዚህ ያለ ወሬ ባወሩ ሰዎች አዝናለው እንጂ ሌላ የምለው ነገር የለም።

“ወደ አሰልጣኝነት ለመመለስ ፍላጎቱ አለኝ። ያው እንደሚታወቀው ቦታው በጉሩፕ ተይዟል። ሰዎች ክለብ የሚይዙት በአቅማቸው አይደለም። እኛን ወደ አሰልጣኝነቱ እንድንመጣ የሚጋብዙ ነገሮች የሉም። እኔ በጣም የማዝነው እኛ ለሀገር ካገለገልነው፣ ከለፋነው አንፃር በክለብም በብሔራዊ ቡድንም ማሰልጠን ነበረብን። ይህ በመሆኑ አዝናለሁ። ወጣት ብሔራዊ ቡድን እኛ ለማሰልጠን መጠራት ሲገባን ሌላ ከየት እንደሚመጣ አናውቅም። አሁን ነው ደሳለኝ ገብረ ጊዮርጊስ ሲጠራ ደስ ያለኝ፤ የኮራሁት። ዝም አልኩኝ እንጂ በተደጋጋሚ የሚጠራው የሚሄደው ሰው አንድ ነው። ስለዚህ ለሀገር የለፋነውን ከግምት አስገብተው ወጣት ቡድን የምንሰራበት መንገድ መመቻቸት አለበት። ፌዴሬሽኑን ስንጠይቅ የአሰልጣኙ ምርጫ ነው ይሉናል። አሰልጣኙ ከመንገድ ላይ የግብጠባቂ አሰልጠኝ ቢመርጥ ሊቀበሉ ነው? ስለዚህ ይህ መስተካከል አለበት። የግብጠባቂ ችግር አለ ይባላል ለምን አይኑር አሰልጣኙ ማነው? ይህ መመለስ አለበት። እኛ ሀገራችንን ማገልገል አለብን እኔ ብቻ አደለሁም ብዙ ለሀገራቸው የሰሩ እንደ ሰብስቤ ሸገሬ፣ እድሉ ደረጄ ሌሎችም አሉ ለሀገራቸው ለፍተው ሰርተፍኬት ይዘው ቤታቸው የተቀመጡ አሉ። ለምን ለእነርሱ አይሰጥም? ይህ ውለታ አይደለም፤ ባለን አቅም እንስራ ነው። ሁሉ ነገር በጉሩፕ መሆኑ መቅረት አለበት።

“ወራቤ ላይ እየሰራነው ያለው ፕሮጀክት ወደ መቶ ሰማንያ የሚጠጉ ታዳጊዎች አሉን። ከስምንት ዓመት ጀምሮ እስከ አስራ ሰባት ዓመት ድረስ ያሉትን ነው የያዝነው። በዕድሜ እና በብቃታቸው እየለየን ወደ ብቃት ያልመጡትን እያሰራን ሀያ አምስት ሀያ አምስት እያደረግን የወዳጅነት ጨዋታ ጀምረናል። በቀጣይ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የተለያዩ ጨዋታዎች በማድረግ የተሻሉ ልጆችን ወደ ተለያዩ ክለቦች እንዲሄዱ ለማድረግ እየሰራን ነው። መብራት ኃይል በዚህ ረገድ መጥቶ ልጆችን ለማየት ፍቃደኛ ሆኗል። በዚህ አጋጣሚ እናመሰግናለን። እንግዲህ ከጋሽ ከማል ጋር በመሆን ወርደን ወራቤ ታዳጊዎች ላይ እየሰራን ነው። ጋሽ ከማል ብዙ አቅም ያላቸው ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ናቸው። እርሳቸውም ወርደው እየሰሩ ነው። እስካሁን ባለው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው የሚገኘው። ለዚህም የስልጤ ህዝብ፣ የሰልጣኝ ወላጆች፣ ወራቤ አስተዳደር፣ ወራቤ ትምህርት መምርያ፣ ወራቤ ዩኒቨርስቲ፣ ወራቤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ ወራቤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እነዚህ ሁሉ ደግፈውን ለሀገር የሚጠቅሙ መልካም ልጆችን እያፈራን እንገኛለን። በዚህ አጋጣሚ ከላይ የጠቀስኳቸውን አካላት በሙሉ አመሰግናለሁ።

የቤተሰብ ህይወቴ ያገባሁ ነኝ። ስሟ ኢክማ ሀሰን ትባላለች። ከእርሷም አንድ ልጅ አለኝ፤ አብዱልከሪም ሳዳት ይባላል። ስድስት ዓመቱ ነው። የምኖረው ሀዋሳ ነው። ልጄም የኔን ፈለግ በመከተል እየሰራ ነው። አሁን ካለው ፕሮጀክት ጋር ቀላቅየው በማሰራት ጥሩ ግብጠባቂ አደርገዋለው ብዬ አስባለው።

“በመጨረሻም ለአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ አሥራት ኃይሌ፣ አብርሀም መብራቱ፣ አብርሃም ተክለሃይማኖት እና ሌሎች አሰልጣኞች ትልቅ ክብር አለኝ። ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ምስጋና አቀርባለሁ። የሀገራችንን እግርኳስ ለማሳደግ ሁሉም የሚመለከተው አካላት በጋራ በመሆን መረባረብ አለበት እላለሁ።


ላለፉት ስምንት ወራት በተለያዩ ዓምዶች ሥር ስናቀርብላችሁ የቆየው መደበኛ ፕሮግራሞች የመጀመርያ ምዕራፍ ተጠናቋል። ወደፊት በሁለተኛ ምዕራፍ በተሻለ ይዘት እና ቅርፅ ወደ እንደምንመለስ እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ