ሶከር ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሊጉ የተሰሙ ዜናዎችን አጠር ባለ መልኩ መረጃዎችን ሰብሰብ በማድረግ ይዛላችሁ ቀርባለች፡፡
– ነቀምቴ ከተማ የተላለፈበትን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ በ2011 በአማካይ ስፍራ ላይ እየተጫወተ የሚገኘው ፍቅርተ ደስታ የ12 ወር የውል ጊዜ እየቀረው በመሰናበቱ እና መሰናበቴ አግባብ አይደለም በሚል ለፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ጉዳዩን ካቀረበ በኃላ ኮሚቴው በነቀምቴ ላይ የእግድ ውሳኔን ከወራት በፊት ያስተላለፈ ሲሆን አሁን ግን ከተጫዋቹ ጋር በተደረገ ስምምነት ውሳኔው መነሳቱን ተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡
– በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ ላይ የተደለደሉ ክለቦች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን “አማካይ ከተማ እያለ ጅማ ላይ ሄዳችሁ ተወዳደሩ መባሉ አግባብ አይደለም፤ ለሌላ ተጨማሪ ወጪ ስለሚያደርገን ይለወጥልን” ሲሉ በማለት የቅሬታ ደብዳቤን አስገብተዋል፡፡ ይሁንና ከፌድሬሽኑ ባገኘነው መረጃ ይህ አቤቱታ ምንም አይነት ለውጥ እንደማይኖረው እና በተያዘለት ዕለት እና ቦታ ውድድሩ እንደሚደረግ አረጋግጠናል፡፡
– ከቀናቶች በፊት የከፍተኛ ሊግ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት የተደረገ ሲሆን በወቅቱ በሚሻሻሉ ደንቦች እና ህጎች ላይ ተጨማሪ ስብሰባ እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን ውድድሩ ከመጀመሩ ከአንድ ሳምንት በፊት ይህ የተሻሻሉ ህጎች እና ደንቦች ላይ በሀዋሳ ለክለቦች ገለፃ እና ማብራሪያ እንደሚደረግ ሰምተናል፡፡
– በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት በቅርቡ ሲደረግ የትግራይ ክልልን ከወከሉ ሦስት ክለቦች ማለትም አክሱም ከተማ፣ ደደቢት እና ሶሎዳ አድዋ በምድብ ሀ ላይ መደልደላቸው ይታወሳል፡፡ በዕለቱ የሶሎዳ አድዋ ክለብ ተወካይ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአቱ ላይ በመገኘት ዕጣ ያወጡ ቢሆንም ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ሦስቱም ክለቦች ከውድድሩ ውጪ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀደም ባለው ድልድል አስራ ሁለት ክለቦች የነበሩ ሲሆን የሦስቱን መውጣት ተከትሎ ቁጥሩ ወደ ዘጠኝ ዝግ ብሏል ይህንንም ተከትሎ የምድብ ለ እና ሐ አንዳንድ ክለቦች ከየምድባቸው ሽግሽግ እንዲደረግላቸው ለፌዴሬሽኑ ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
– ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ2009 አድጎ መወዳደር የቻለው ጅማ አባቡና የመፍረስ ስጋት ተደቅኖበታል፡፡ በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች እና ተጫዋቾች ለድረገፃችን “ምንም አይነት የተሳትፎ እንቅስቃሴ ክለቡ እያደረገ አይደለም። ውል ያለን ተጫዋቾች አለን። እስከ አሁንም ደመወዝ አላገኘንም” ሲሉ ነግረውናል፡፡ እኛም ከሰማነው ቅሬታ ተነስተን በዋናነት ክለቡ ዘንድሮ ይቀጥላል ወይንስ አይቀጥልም የሚለውን ጉዳይ ለማረጋገጥ ለጅማ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እና የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጉተማ መኮንን ጥያቄ ብናቀርብም በምላሻቸው ስለ ክለቡ ምንም ነገር እንደማያውቁ እና መልስ መስጠት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ለክለቡ ቅርብ ከሆኑ ሰዎች ባገኘነው መረጃ ክለቡ የመቀጠሉ ነገር ሙሉ ለሙሉ እንዳበቃለት እና ምንም ነገሮች እየተሰሩ እንዳልሆነ አረጋግጠውልናል፡፡
– የወልዲያ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለከፍተኛ ሊጉ ውድድር ተመርጦ የነበረ ቢሆንም በሒደት እንዳያስተናግድ መሆኑ እና የቦታ ለውጥ መደረጉ ቅሬታን እንደፈጠረ ክለቡ ገልጿል፡፡ በተለይ ከየትኛውም የተሻለ ዓለም አቀፍ ሜዳ ሆኖ ሳለ ወልዲያ የጦርነት ከተማ ስለሆነች በሚል ባልተረጋገጠ መረጃ ይሄ መሆኑ አሳዝኖናል ሲሉ አቶ ይመር አበባው የወልድያ ስታዲየም ስራ አስኪያጅ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ “የወልዲያ ስታዲየም ከፍተኛ ሊጉን እንደሚያስተናግደው ተገልፆልን በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ ስሜት ተፈጥሮ ነበር። ግን ውድድሩ ወደ ባቱ መዛወሩን ስንሰማ ቡድኑን ላለመሳተፍ ወስነን ነበር። ከወልዲያ አካባቢ ካሉ አመራሮች እና የደህንነት አካላት ምንም መረጃን ሳያገኝ የወልዲያ ከተማ የጦርነት ቀጠና ነው በሚል ምክንያት ቦታ መቀየሩ ምንም የሚያስማማ ሀሳብ አይደለም። ይሄ በመሆኑ ህብረተሰቡ አካባቢ ጥሩ ስሜት የለም። ይሄ ሁሉ ወጪ ወጥቶ ተገንብቶ ለውድድር ብቁ የሆነን ሜዳ አለመምረጥ ይሄንን ሜዳ መገንባታችን ስህተት ነው እንድንል አስገድዶናል። በፌዴሬሽኑ አሰራርም አዝነናል” ብለዋል፡፡
-በአንጋፋው ተጫዋች ታፈሰ ተስፋዬ ተከሰው የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሙሉ በሙሉ የነበረበትን የስድስት ወር የደመወዝ ክፍያ ሙሉ በሙሉ መፈፀማቸው ተገልጿል፡፡ ከነሀሴ 2011 እስከ ጥር 30 / 2012 ድረስ ተጫዋቹ በክለቡ ውል እያለኝ መሰናበቴ ተገቢ አደለም በማለት ጉዳዩን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በክስ መልክ በማቅረቡ ፌድሬሽኑ በክለቡ ላይ የእግድ ውሳኔን አስተላልፎ ቆይቷል ሆኖም ክለቡ እና ተጫዋቹ የገቡበትን እሰጣ ገባ የፈቱ ሲሆን ክለቡ የተጠየቀውን ሙሉ ክፍያ በውሉ መሠረት ተፈጻሚ አድርጓል፡፡
– በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ላይ የሚገኘው ወሎ ኮምቦልቻ ያለበትን የገቢ ችግር ለመቅረፍ ኮሚቴ ማቋቋሙን የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ለድረ ገፃችን ገልጸዋል፡፡ ክለቡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ይታይበት የነበረውን ደመወዝ የመክፈል ችግር ከስሩ ቀርፎ ለመጣል በማሰብ ኮሚቴን አዋቅሮ ከከተማው እና አካባቢው ማህበረሰብ እና ባለ ሀብቶች ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ገቢ እንደሚሰበስብ ሀላፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ