በመጀመሪያ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትኩረት የሳቡ ተጨማሪ የመጀመሪያ ሳምንት ጉዳዮች በዚህ ፅሁፍ ተዳሰዋል።
👉ሊጉን የተለየ ገፅታ ያላበሰው የቴሌቪዥን ስርጭት
የዘንድሮውን የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከእስከ ዛሬዎቹ ለየት የሚያደርገው ዋነኛ ጉዳይ ለዓመታት ገቢ ማመንጨት ተስኖት የነበረው የሀገራችን የክለቦች የእግርኳስ ውድድር ዘንድሮ በተለየ መልክ ገቢ ማመንጨት የመጀመሩ ጉዳይ ነው። ከዚህ ገቢ ጀርባ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ሊጉ ከመልቲ ቾይዝ አፍሪካ ጋር ጨዋታውን ለማስተላለፍ የፈፀመው የውል ስምምነት ነው።
ይህን ተከትሎ በበርካቶች ዘንድ ሊጋችን በመሰል የፕሮዳክሽን ጥራታቸው በላቁ ጣቢያዎች ሲተላለፍ ምን ይመስላል የሚለው በበርካቶች ዘንድ ሲጠበቅ የነበረ ጉዳይ ነበር። ለዘመናት በርካቶች ይጓጉለት የነበረው ይህ ቀን ደርሶም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በሱፐር ስፖርት መተላለፍ መጀመሩ በትልቁ የሚነሳ ጉዳይ ነው።
👉የድሬዳዋ ከተማ መለያ ጉዳይ
በዘንድሮው የውድድር ዘመን የሊጉ ውድድር በቴሌቪዥን መተላለፉን ተከትሎ ለወትሮው ከብራንዲንግ እና ተያያዥ ጉዳዮች ሩቅ ለሆኑት የሀገራችን ክለቦች የተሻለ ነገር ይዞ ይመጣል ተብሎ ተጠብቋል።
ለወትሮው በብርቱካናማ እና በነጭ ቀለማቸው የሚታወቁት ድሬዳዋ ከተማዎች ዘንድሮ ደግሞ በወርቃማ ቀለም መለያ ብቅ ብለዋል። በበርካታ ደጋፊዎች ዘንድ ተቀባይነት የነበረው ነጭ በብርቱካናማ (ዳማ) መለያን አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ከተቀየረ ወዲህ አምና በመጀመሪያ ተመራጭነት ሙሉ ብርቱካናማ እንዲሁም በሁለተኛነት ደግሞ ነጭ መለያን በውሃ ሰማያዊ ቁምጣ ይጠቀም የነበረው ቡድኑ ዘንድሮ ደግሞ በአሸዋማ ቀለም መለያ እና ሰማያዊ በነጭ ቁምጣ ብቅ ብለዋል።
የሀገራችን ክለብ አመራሮች ክለባዊ ማንነትን ለመገንባት መሰረታዊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ወጥ የሆኑ የመለያ ቀለሞችን መጠቀም ላይ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። በድሬዳዋ ከተማም በኩል መሰል ችግሮች ይስተዋላሉ።
በቅዳሜው ጨዋታ ክለቡ የተጠቀመበት መለያ ዙርያ በወቅቱ ጨዋታውን ለመከታተል ሜዳ የተገኙትን የተወሰኑ ቁጥር ያላቸውን የክለቡ ደጋፊዎችን ጨምሮ በርካቶችን ግራ ያጋባ እና አግራሞትን የሚያጭር ጉዳይ ነው።
👉የክለቦች መለያ አመራረጥ
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተካፈሉ የሚገኙ ክለቦች በአመዛኙ በትዕዛዝ የክለባቸውን መለያ ቀለሞች ባማከለ መልኩ መለያዎችን በራሳቸው መገለጫ መሠረት ማሰራት እየተለመደ መጥቷል። ቢሆንም ግን አሁንም ቢሆን በአብዛኛዎቹ ክለቦች ዘንድ ትኩረት የሚሰጠው ስለ መጀመሪያ ተመራጭ መለያ እንጂ ሰለ አማራጭ ሁለተኛ እና ሦስተኛ መለያዎች ትኩረት ሲደረግ አይስዋልም።
ይልቁንም ክለቦች የበረኛ እና አማራጭ መለያዎችን በቀላሉ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የስፖርት ትጥቅ መሻጫ ሱቆች ላይ የሚገኙ በዲዛይንም ሆነ በቀለም ስብጥር የሚመሳሰሉ መለያዎችን ሲጠቀሙ ይስተዋላል። በዚህም በዋናው ማልያ ላይ የሚታዩ የቁጥር፣ የሎጎ እና የፅሁፍ ስብጥሮች በሌሎቹ ማልያዎች ላይ ሴይቴዩ ወይም በሌላ አቀማመጥ ሲቀመጡ ጉልህ ይስተዋላሉ። በዚህኛው ሳምንትም ለማሳያነት ሀዲያ ሆሳዕና፣ አዳማ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር የተጠቀሙባቸው መለያዎች የዚህ ነፀብራቅ ናቸው።
በመሆኑም መሰል ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን ትልቅ ተፅዕኖ ያላቸው ጉዳዮች በክለቦቻችን ረገድ ልብ ሊባሉ ይገባል።
👉 የማልያ ስታንዳርድ አስፈላጊነት
ከማልያ ጋር በተለያያዘ ሌላው የሚነሳው ነጥብ ሊጉ የቴሌቪዥን ስርጭት በማግኘቱ ምክንያት በተጫዋቾች ጀርባ ላይ ስማቸው እንዲቀመጥ መደረጉ ነው። ይህ እንደ ጅማሮ መልካም ቢሆንም በአንደኛው ሳምንት እንደታየው በማልያዎቹ ላይ የታተሙት ስሞች አመዛኞቹ ከማልያው ቀለም ጋር የተመቻቸ ስብጥር የሌላቸው፣ በጉልህ የማይታዩ፣ የመጠን (Font size) መመጣጠን የማይታይባቸው ከክለብ ስም ጋር በጋራ የተቀመጡ፣ ከነአካቴው ስም ያልተፃፈባቸው እና መሰል ግድፈቶች ታይቶባቸዋል። የሊጉ ባጅ የሚቀመጥበት ስፍራም እንደየ ቡድኖቹ ሲለያይ ተመልክተናል (የአንዳንዶቹ በደረት፣ የአንዳንዶቹ በክርን አካባቢ ተለጥፈው ታይተዋል)
በእርግጥ ይህ ልማድ ዘንድሮ የተጀመረ ከመሆኑ አንፃር በቀጣይ እንደሚስተካከል የሚታመን ቢሆንም የሊጉ አስተዳደር በዚህ ዙርያ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ክለቦች ሊጠቀሙበት የሚገባ የማልያ ስታንዳርድ በመመርያ መልክ አዘጋጅቶ ሊተገብር ይገባል። የሊጉ ባጅ አቀማመጥ፣ የማልያ ስፖንሰሮች አቀማመጥ፣ የማልያ ቁጥር መጠን እና የቀለም ስብጥር፣ የተጫዋች ስም መጠን እና የቀለም ስብጥር እና የመሳሰሉት ወጥነት ከግምት ሊገቡም ይገባል።
👉ትኩረት የሚሻው ድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቅ
የሊጉን የቴሌቪዥን ስርጭት መብቱ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከጨዋታዎች መጠናቀቅ በኃላ የሚሰጡ ድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቆች በብቸኝነት የማሰራጨት መብቱን ለገዛው ሱፐር ስፖርት የተሰጡ ናቸው ፤ ይህም ከፍተኛ ተከታታይ ባላቸው የአውሮፓ ሊጎችም ቢሆን የተለመደ አሰራር ነው።
ነገርግን ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ከሚሰጡት አጫጭር ቃለ መጠይቆች መጠናቀቅ በኃላ ግን ለሁሉም ሚዲያ አባላት ክፍት የሆነ ድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቆች ይደረጋሉ ፤ ይህም ለሌሎች የሚድያ አባላት ከጨዋታው መነሻነት ለዜናነት ግብአት ይሆኑናል ባሏቸው ጉዳዮች ዙርያ ማንሳት በፈለጓቸው ጉዳዮች ዙርያ ከአሰልጣኞች ቡድን አባላት ማብራሪያን የሚያገኙበት ሂደትን ይፈጥራል።
የመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ያስመለከተን ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው ስለዚህ መሰል ለሁሉም ክፍት የሆነ ቃለ መጠይቆች መጀመር ይኖርባቸዋል ፤ ምንም እንኳን ገና ይህ ልምምድ ለሀገራችን አዲስ ቢሆንም በቀጣይ ግን መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል።
👉 የኮቪድ ፕሮቶኮል እና የተመልካች ስታዲየም መግባት
ውድድሮች በመላ ሀገሪቱ እንዲጀመሩ በተሰጠው ፈቃድ መሰረት የሚመለከታቸው አካላት የኮቪድ ፕሮቶኮልን ተከትለው ውድድሩን ማስኬድ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ሲገለፅ ሰንብቷል። ከመመርያዎቹ መካከል ተመልካች ወደ ስታዲየም መግባትን የሚከለክለው ደንብ የሚጠቀስ ቢሆንም ጥቂት ተመልካቾች ጨዋታዎችን ሲታደሙ እየተመለከትን እንገኛለን። የውስን ተመልካች ወደ ስታዲየም መግባት በሀገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር መጥፎ ባይባልም የሚገቡ ተመልካቾች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መከታተል ላይ ግን ክፍተቶች ታይተዋል። ተጠጋግተው የመቀመጥ፣ ተያይዘው ደስታቸውን የመግለፅ እና መሰል ሁነቶች መስተዋላቸው የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ