የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባሳለፍነው ቅዳሜ ጅማሮውን አድርጓል። በበርካታ መመዘኛዎች ከወትሮው የተለየው የዘንድሮው የውድድር ዘመን በ13 ክለቦች መካከል መደረጉን ጀምሯል። እኛም በጨዋታ ሳምንት አንድ ትኩረት የሳቡ ክለብ ነክ ጉዳዮችን በዚህ ፅሁፍ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
👉የተለወጠው ሰበታ ከተማ

በተሰረዘው የውድድር ዘመን በርከት ያሉ በሊጉ በመጫወት የካበተ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች ተሞልቶ የነበረው የሰበታ ከተማ ስብስብ አዲሱ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በተወሰነ መልኩ ለማሻሻል በዝውውር መስኮቱ የሰሩት ሥራ በመጀመሪያው ሳምንት በጉልህ ተስተውሏል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቡድኑ ዐምና ከነበረው ስብስብ በርካታ ተጫዋቾችን ለቀው በንፅፅር የቡድኑን አማካይ የተጫዋቾችን ዕድሜ ሊያወርዱ የሚችሉ ወጣት ተጫዋቾች ተቀላቅለውበት ተስተውሏል። በዚህም ቡድኑ ከድሬዳዋ ከተማ አቻ በተለያየበት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ዐምና በአመዛኙ ይጠቀምበት ከነበረው የቡድን ስብስብ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾችን ከወጣቶች በቀላቀለ መልኩ ወደ ጨዋታ ቀርቧል።

ምንም እንኳን አብርሃም መብራቱ የተከተሉት የቡድን ግንባታ ሒደት በቀጣይ በተከታታይ ሜዳ ላይ በሚመዘገብ ውጤት የሚለካ ቢሆንም ዐምና ዘለግ ላለ የጨዋታ ደቂቃ በወጥነት ለመንቀሳቀስ ይቸገር የነበረውን ስብስብ አይነተኛ ለውጥ ለማምጣት በጥሩ ሒደት ላይ ስለመሆኑ ፍንጭ የሰጠ ጨዋታ ነበር።

👉ተስፋ ያልቆረጡት “ሠራተኞቹ”

በአቡበከር ናስር ሁለት ግቦች በኢትዮጵያ ቡና እስከ 74ኛው ደቂቃ ድረስ 2-0 ሲመሩ የቆዩት ወልቂጤ ከተማዎች ተቀይሮ በገባው ያሬድ ታደሰ እና ረመዳን የሱፍ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች ከመመራት ተነስተው አንድ ነጥብ ለመጋራት በቅተዋል።

ዐምና ተለዋዋጭ የጨዋታ አቀራረብ እና ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት መለያው የነበረው የደግአረግ ይግዛው ስብስብ ከመመራት ተነስቶ ሁለት ግቦችን ማስቆጠሩ በተጫዋቾቹ ዘንድ ያለውን ጠንካራ የአዕምሮ ዝግጅት ደረጃ ከማሳየት በዘለለ ዕድሎችን ለመፍጠር እና በጨዋታዎች ከአንድ በላይ ግብን ለማስቆጠር ይቸገር የነበረው ቡድኑ በክረምቱ ይህን ችግር ለመቅረፍ ያደረጋቸው የተጫዋቾች ዝውውር መፍትሄ ሊያመጡ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነበር።

👉አስቀድሞ ወደ ውድድር በመግባቱ የተጠቀመው ፋሲል

ከሊጉ መጀመር አስቀድሞ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከዩኤስ ሞናስቲር ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ የነበረው ፋሲል ከተማ ከሌሎች ቡድኖች በተሻለ በሊጉ የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት እንደ ቡድን የተደራጀ እንቅስቃሴን ከማሳየት በዘለለ ጠንካራውን ቅዱስ ጊዮርጊስን 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን በድል ከፍቷል።

የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ስብስብ ከተቀሩት አስራ ሁለት የሊግ ክለቦች በተሻለ አስቀድሞ ሁለት የፉክክር ጨዋታዎችን ከሀገራች ክለቦች በደረጃው ላቅ ካለው የቱኒዚያ ቡድን ጋር ማድረጉ በተለይ ሌሎቹ ክለቦች ይህ ነው የሚባል የወዳጅነት ጨዋታዎችን ካለማድረጋቸው ጋር ተዳምሮ ፋሲል ከተማ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት በሊጉ እጅግ የተሻለው ቡድን እንዲሆን ያስችሉታል ተብሎ ይጠበቃል።

👉ከምንም እየተገነባ የሚገኘው አዳማ

ላለፉት ጥቂት ዓመታት በሊጉ በወጥነት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደርጉ ከነበሩ ክለቦች አንዱ የነበረው አዳማ ከተማ ዘንድሮ ግን በርከት ያሉ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾችን በዝውውር መስኮቱ በተለይም በሀዲያ ሆሳዕና እና ሌሎች ክለቦች መነጠቃቸውን ተከትሎ ቡድናቸውን በአሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል ዳግም ከምንም በመነሳት በማደራጀት ላይ ይገኛሉ።

ባሳለፍነው እሁድም ቡድኑ በመክፈቻው የሊጉ መርሃግብር ጅማ አባጅፋርን 4-1 መርታት ሲችሉ ፤ በዚህም ለጨዋታው ካስመዘገቡት የጨዋታ ዕለት ስብስብ ውስጥ ሁለት ተጫዋቾች ብቻ ዐምና ከነበረው የቡድኑ ስብስብ አባል የነበሩ መሆኑናቸውን ከግምት ስናስገባ የግንባታው ሒደት ምን ያህል ከባድ መሆኑን ለመረዳት አይከብድም።

ለሊጉ አዳዲስ በሆኑ እና የተወሰኑ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በማቀናጀት እየተገነባ የሚገኘው የአሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል ስብስብ ምንም እንኳን የውድድር ዓመቱ ጉዞ ረጅም ቢሆንም በመጀመሪያው ሳምንት ያስመዘገቡት የ4-1 ድል የቡድኑን የራስ መተማመን ከፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉አዳማ + ሆሳዕና ” አዳዕና “

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከአዳማ ከተማ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ማምራት ተከትሎ በርካታ የቀድሞ አዳማ ከተማ ተጫዋቾች በዝውውር መስኮቱ መዳረሻቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክለችተጫዋችን ሆሳዕና ማድረጋቸው የክረምቱ የዝውውር መስኮት ዋነኛው ርዕሰ ዜና እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነበር።

በመጀመሪያው ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕና ወላይታ ድቻን 2ለ1 ሲረታ አምስት የቀድሞ የአዳማ ተጫዋቾችን በመጀመሪያ 11 በመግባት ለሆሳዕና የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በቋሚነት በመጀመር ማድረግ ችለዋል። በጨዋታውም ሁለቱም የማሸነፍያ ግቦች የተገኙት በቀድሞዎቹ የአዳማ ከተማ ተጫዋች ዳዋ ሆቴሳ እና ተቀይሮ በገባው ዱላ ሙላቱ መሆኑ ደግሞ ግጥጥሞሹን አስገራሚ ያደርገዋል።

👉ከፈረሱት በተሻለ፤ ካሉት እጅጉን በወረደ ደረጃ ላይ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊዎቹ ጅማ አባጅፋሮች አሁናዊ ሁኔታ ከፈረሱት ክለቦች በተሻለ እንዲሁም እየተወዳደሩ ካሉ ክለቦች ደግሞ እጅጉን በወረደ ደረጃ ላይ ይገኛል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ላለፉት ሁለት ዓመታት የዘለቀው የክለቡ ችግር አሁን ድረስ እንደቀጠለም ይገኛል።

በአሉታዊ ጉዳዮች ርዕሰ ዜና መፍጠሩን የቀጠለው ቡድኑ በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ያለ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ የቡድናቸው ግብጠባቂ በ8ኛው ደቂቃ በቀጥታ ቀይ ካርድ መውጣቱን ተከትሎ የሜዳ ላይ ተጫዋችን በግብ ጠባቂነት ለመጠቀም መገደዱ እጅግ አነጋጋሪ የሆነ ክስተት ነበር።

ክለቡ በክረምቱ በደጋፊዎች ዘንድ እጅግ ተስፋ የተጣለበት የአመራር ለውጥ ቢያደርግም ነገሮች እስካሁን ድረስ ወደ በጎ መለወጥ አልቻሉም። ክለቡ ከገባበት ከዚህ አዙሪት መች ይላቀቃል የሚለው ጉዳይም ይጠበቃል።

👉ከዐምናው የቀጠለው የኢትዮጵያ ቡና “ፕሮጀክት”

ለሁለት አስርት ዓመታት ከቀረበ የሀገር ውጭ ቆይታ በኋላ በደጋፊዎች እጅግ ሲናፈቅ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና እና የካሳዬ ጋብቻ ከተፈፀመ ይሄው ሁለተኛ የውድድር ዘመኑ ላይ ደርሷል።

ምንም እንኳን የተሰረዘውን የውድድር ዘመን ለአሰልጣኙ እንደ ጥሩ የሙከራ ጊዜ ቢታይም ዘንድሮ ሁለተኛ የውድድር ዘመን እንደመሆኑ በደጋፊዎች ዘንድ ከአምናው የተሻለ የውጤት ጉጉት እንደሚኖር ይጠበቃል። ከዐምናው ስብስብ በጥቂቱ የተቀየረው ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ ከወልቂጤ ከተማ ጋር በእጁ የገባውን ድል አሳልፎ ሰጥቶ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

በአጨዋወት ደረጃ ምንም እንኳን በአንድ ጨዋታ ብቻ መገምገም ለስህተት ሊዳርግ ቢችልም እንደ ዐምናው ሁሉ በኳስ ምስረታ ሒደት ላይ በቁጥር አነስተኛ በሆኑ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ጫና ስህተቶች መሥራት በተለይ በወልቂጤው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በስፋት የተስተዋለ ችግር ነው። መሰል ጫናዎችን ተቋቋሞ መጫወት በተደጋጋሚ ልምምዶች የሚዳብር ቢሆንም በንፅፅር አነስተኛ በሆኑ ጫናዎች ውስጥ ስህተቶች መብዛታቸው ግን ትኩረትን የሚሻ ይመስላል።

👉ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮም?

ከዚህ በፊት ባልተከሰተ ሁኔታ በሁለት ተከታታይ ዓመታት ዋንጫ ያጡት ፈረሰኞቹ በተሰረዘው የውድድር ዓመትም ወጣ ገባ አቋም ሲያሳዩ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮም ከጅማሬው በዋነኛ የዋንጫ ተፎካካሪው ፋሲል ከነማ ሽንፈት አስተናግዋል። ቡድኑ የማጥቃት ኃይሉን ለማጠናከር በሊጉ ድንቅ የሚባሉትን ተጫዋቾች ቢያዘዋውርም ቀስ በቀስ እየራቀው የሚገኘው የአሸናፊነት ስነ-ልቦና እና ለውጤት ተጠባቂነት የሚፈጥረው ጫና አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረበት እንደሆነ እየታየ ይገኛል።

በስብስብ ደረጃ ይህ ቀረው የማይባለው ቡድኑ ወደ ቀደመው ከፍታው ለመመለስ ከተጫዋች ጥራት በላይ በመሠረታዊነት የተጫዋቾቹ ስነ ልቦና ላይ ሥራዎች ይጠበቁበታል። ምንም እንኳን የመጀመሪያ ጨዋታ እንደመሆኑ በቀጣይ ብዙ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ ቢታመንንም ጊዜያዊ አሰልጣኙ ማሄር ይህን ጥራት ባላቸው ተጫዋቾች የተሞላውን ስብስብ ወደ ቀደመ ክብሩ የመመለስ ከፍተኛ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ