ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ1ኛ ሳምንት ምርጥ 11

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ 2013 የውድድር ዘመን ከቅዳሜ እስከ ሰኞ በተደረጉ ጨዋታዎች መጀመሩ ይታወሳል። በተካሄዱት ስድስት ጨዋታዎች ላይ ተመስርተን የሳምንቱ ምርጥ አስራ አንድ እና ምርጥ አሰልጣኝ እንደሚከተለው መርጠናል።

አሰላለፍ: 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ፋሲል ገብረሚካኤል (ሰበታ ከተማ)

በጨዋታ ሳምንቱ ግብ ሳያስተናግዱ ከወጡ ሦስት ቡድኖች መካከል ሰበታ ከተማ አንዱ ነው። ከሦስቱ ቡድኖች በርካታ ሙከራ የተደረገበትም እንዲሁ ሰበታ ከተማ ነው። ፍፁም ቅጣት ምትን ጨምሮ ኢላማቸውን የጠበቁ በርካታ ኳሶችን በማዳን ቡድኑ ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ ወሳኙን ሚና የተወጣው ደግሞ ወጣቱ ግብ ጠባቂ ፋሲል መሆኑ ምርጫውን አስማሚ ያደርገዋል።

ተከላካዮች

ታፈሰ ሰርካ (አዳማ ከተማ)

ምንም እንኳ የአዳማ ተጋጣሚ ጅማ አባ ጅፋር አንድ ተጫዋች ወጥቶበት አብዛኛውን ደቂቃ ለመጨረስ ቢገደድም የታፈሰ የጨዋታው እንቅስቃሴ ግን ድንቅ ነበር። ተጫዋቹ አብዛኛውን ደቂቃዎች በማጥቃት ወረዳ ላይ በመገኘት በርካታ ሙከራዎችን ከማድረጉ ባሻገር በፍፁም ቅጣት ምት እና በጨዋታ ሁለት ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል።

ከድር ኩሊባሊ (ፋሲል ከነማ)

ኮትዲቫራዊው የቀድሞው የደደቢት ተከላካይ በዐፄዎቹ ቤት ወሳኝነቱ ቀጥሏል። ከያሬድ ባየህ ጋር በፈጠረው ጥምረት ከሀብታሙ ተከስተ እና ይሁን እንዳሻው ሽፋን ጋር ተደምሮ የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ክፍተት እንዳያገኝ በማድረግ እና በአንድ ለአንድ ግንኘነቶች ወቅት ባለው ጥንቁቅነት በዚህ ሳምንት በቦታው ተመራጭ ሆኗል።

መናፍ ዓወል (ባህር ዳር ከተማ)

ባህር ዳር እንደቡድን ጥሩ በተንቀሳቀሰበት የሲዳማው ጨዋታ ላይ መናፍ ያደረገው እንቅስቃሴ የቡድኑ ቁልፍ ፈራሚ ስለመሆኑም የሚያረጋግጥ ነበር። ከሰለሞንን ወዴሳ ጋር በፈጠረው ጥምረት ለኋላ ክፍሉ እርጋታን በመጨመር እና አጥቂዎችን በመቆጣጠር ጥሩ 90 ደቂቃ አሳልፏል።

ኢዮብ ማቲዮስ (አዳማ ከተማ)

የሳምንቱ ምርጫ እጅግ ከባድ የሆነው እዚህ ቦታ ላይ ነው። ሌላኛው ድንቅ ብቃት ያሳየው የወልቂጤው የመስመር ተከላካይ ረመዳን የሱፍ ጋር ኢዮብ ያደረገው እንቅስቃሴ ምርጫውን አሻሚ ያደርገዋል። እዮብ በጨዋታው ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ በሙሉው የጨዋታ ጊዜ ወጥ የሆነ ብቃት አሳይቷል።

አማካዮች

ሀብታሙ ተከስተ (ፋሲል ከነማ)

የቅዱስ ጊዮርጊስ አማካዮች የኳስ ቁጥጥር እና መሀል ለመሀል የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ባማቋረጥ ሀብታሙ ጥሩ ጨዋታን አሳልፏል። ኳስ ከማስጣል በተጨማሪ ተጫዋቾችን በግል ብቃቱ በማለፍ እና የተሳኩ ቅብብሎችን በመከወን የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ የማስጀመር ኃላፊነቱን የተዋጣበት ሳምንትን አሳልፏል።

አዲስ ህንፃ (ሀዲያ ሆሳዕና)

ሀዲያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስቶ ወደ ጨዋታው ምት እንዲገባ የመሀል ክፍሉን በእርጋታ የሚመራ አማካይ ያስፈልገው ነበር። ይህንን ኃላፊነት ልምድ ያለው አዲስ በአግባቡ ተወጥቶታል። የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ለአጥቂዎች የሚደርሱ ኳሶችን ከማሳለጥ ባለፈ አንድ ያለቀለት የግብ ዕድልንም መፍጠር ችሎ ነበር።

ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

ምንም እንኳን ፍፁም በጉዳት ሳቢያ ሙሉ ጨዋታውን መጨረስ ባይችልም ሜዳ ላይ በነበረባቸው 48 ደቂቃዎች ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ቡድኑን አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ማስቀመጥ ችሏል። ግቦቹ ላይ የግል ክህሎቱ በግልፅ የተንፀባረቀባቸው ከመሆኑ ባሻገር ሰፊ ቦታን በመሸፈን በልበ ሙሉነት ሲንቀሳቀስ ተመልክተነዋል።

አጥቂዎች

አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)

አቡበከር የብስለት ደረጃው ከፍ እያለ መምጣቱን እና አሁንም የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን ያሳየበትን ብቃት አሳይቷል። የአካል ብቃት ዝግጁነቱን በሚያሳዩ ቅፅበቶች ቡድኑ ከግራ መስመር የሚሰነዝራቸውን ጥቃቶች በፍጥነት እና በጥሩ እይታው በመምራት ልዩነት ለመፍጠር ሲታትር ታይቷል። ከዚህ ውጪ በፍፁም ቅጣት ምት እና በጨዋታ ሁለት ግቦችን ማስቆጠሩ ለውሎው መልካምነት ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

ዳዋ ሆቴሳ (ሀዲያ ሆሳዕና)

አንድ የቅጣት ምት ጎል አስቆጥሮ ቀጣይዋን የቡድኑን የማሸነፊያ ግብ ያመቻቸው ዳዋ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜውን ድንቅ ነበር። ከግራ ወደ መሀል እየገባ ኳሶችን የሚቀበልበት እና ከርቀት የሚሞክርበት መንገድ ያለበትን የአካል ብቃት እና የራስ መተማመን ደረጃ ከማመላከቱ ባሻገር የድቻ የኋላ ክፍል እንዳይረጋጋ ሲያደርግ መዋሉ ለድሉ ከማንም በፊት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ያደርገዋል።

ባዬ ገዛኸኝ (ባህር ዳር ከተማ)

የባዬ የጨዋታ ዝግጁነት ፣ ተነሳሽነት እና የአካል ብቃት ደረጃ ግብ ሲያስቆጥር ሳይሆን ከጨዋታው መጀመሪያ ጀምሮ በግልፅ የሚታይ ነበር። ወደ ኋላ ተስቦ ከአማካዮች ጋር ቅብብሎችን በመከወን ጨራሽ ብቻ አለመሆኑን ከማሳየቱ ባለፈ ፍፁም ያስቆጠረው ሁለተኛ ግብ ላይም የመጨረሻውን ኳስ በማቀበል እገዛ አድርጓል።

ተጠባባቂዎች

ሀሪሰን ሄሱ (ባህር ዳር ከተማ)

ተስፋዬ ነጋሽ (ወልቂጤ ከተማ)

ረመዳን የሱፍ (ወልቂጤ ከተማ)

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

አብዱልከሪም ወርቁ (ወልቂጤ ከተማ)

በቃሉ ገነነ (አዳማ ከተማ)

ጁኒያስ ናንጂቡ (ድሬዳዋ ከተማ)

አብዲሳ ጀማል (አዳማ ከተማ)

የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ

የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን ባህር ዳር ከተማ ከጨዋታ ብልጫ ጋር 3-1 ከማሸፉ ባሻገር የተረጋጋ እና በሙሉ ጨዋታው ወጥ የሚባል እንቅስቃሴ አድርጓል። ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ፍፁም ዓለሙ ተጎድቶ ሲወጣም ውጤታማ ቅያሪን በማድረግ የቡድኑ የማጥቃት ጉልበት ሳይቀንስ እንዲቀጥል የአሰልጣኝ ፋሲል ውሳኔ አሰጣጥ ትልቅ ድርሻ ነበረው።


© ሶከር ኢትዮጵያ