በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ስድስት ጨዋታዎች የሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴ ላይ በመመስረት ተከታዮቹን ሀሳቦች አንስተናል።
የሀዲያ ሆሳዕና የግራ መስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ…
ሀዲያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረገው ጨዋታ ከመመራት ተነስቶ አሸንፎ መውጣት ችሏል። በዚህ የውጤት ለውጥ ውስጥ የዳዋ ሆቴሳ ሚና እጅግ የጎላ ነበር። የዳዋን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከፍ እንዲል ያደረገው የማጥቃት ስትራቴጂ ደግሞ ይበልጥ ትኩረትን ይስባል። ዳዋ ድቻዎች ኳስ መስርተው በሚወጡባቸው እና ሀዲያ ሆሳዕና ከኳስ ውጪ በሚሆንባቸው አጋጣሚዎች የግራ መስመር አጥቂነት ሚና ይዞ ጨዋታውን መጀመሩ በግልፅ ይታይ ነበር። ሆኖም ቡድኑ በማጥቃት ሂደት ላይ ሲሆን ዳዋ ከግራ በመነሳት ቅብብሎችን እየከወነ እና ኳስን እየነዳ በተደጋጋሚ በሳጥኑ ጠርዝ ላይ በመገኘት የተደራቢ አጥቂ ዓይነት ሚና ኖሮት ይታይ ነበር። ይህም ከሳጥን ውጪ ኳሶችን እንዲሞክር ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ ራሱ ወደ ግብነት የቀየረው የቅጣት ምትም የተገኘው እዚሁ ቦታ ላይ በተሰራበት ጥፋት መነሻነት ነበር። ዳዋ ወደ መሀል በሚገባበት ወቅት የድቻን የተከላካይ መስመር ወደ ቀኝ እንዲያዘነብል በማድረጉም በግራው ኮሪደር ላይ ለአማካይነት ቀርቦ ከበስተኋላው ለተሰለፈው ፈጣኑ መድኃኔ ብርሀኔ ክፍት የመሮጫ ቦታን ያስገኝለት ነበር። በእርግጥ መድኃኔ ራሱን ዝግጁ አድርጎ በቦታው ላይ ቀጥተኛ ሩጫዎችን በማድረግ በተደጋጋሚ ቦታው ላይ ቢገኝም በቂ የኳስ አቅርቦትን ባለማግኘቱ የተገኘውን ክፍተት በሙከራዎች ለማጀብ ዕድሉ አልነበረም። የዳዋ እንቅስቃሴ በራሱ ግን ለሌላ ተጫዋች ክፍተት ከመስጠት፣ የተጋጣሚን የኋላ ክፍል እና ከፊቱ ያለው የአማካዮች ጥምረት ሽፋኑን ከማዛባት በተጨማሪ ለጎል መገኘትም ምክንያት መሆኑ የስትራቴጂውን ውጤታማነት የሚያሳይ ነበር።
የመስመር ተከላካዮች ተፅዕኖ…
በመጀመርያ ሳምንት በተደረጉት ጨዋታዎች የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ሚና ጎልቶ የወጣበት ነበር ማለት ይቻላል። የአዳማዎቹ ታፈሰ ሰርካ እና እዮብ ማቲዎስ ሁለት ጎል በማስቆጠር እና ሁለት ጎል የሆኑ ኳሶችን በማቀበል በቡድናቸው የማጥቃት ሒደት ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊነታቸውን አረጋግጠዋል። ታፈሰ ሰሰርካ እስከተቃራኒ ቡድን ሳጥን ድረስ በመዝለቅ ቀጥተኛ ሙከራዎችን ሲያደርግ የነበረ ሲሆን እዮብ በበከሉ የመከላከል ሚዛኑን ከመጠበቅ ባለፈ ወደ ፊት ገፍቶ በመሄድ የመጨረሻ ኳሶችን ወደ ውስጥ በመጣል ጥሩ ተንቀሳቅሷል። የወልቂጤ ከተማው ረመዳን የሱፍ በበኩሉ ከቀጥተኛ የመስመር ሩጫዎች ይልቅ ወደ ሳጥን ውስጥ ለመግባት የሚያደርገው ጥረት በቀጥታ ከአጥቂዎች ጋር በኳስ ንክኪዎች እንዲገናኝ ከዚያም አልፎ ግብ እንዲያስቆጥር አድርጎታል። የባህርዳር ከተማዎቹ ሚኪያስ ግርማ እና አህመድ ረሺድም የተመጣጠነ የማጥቃት እና የመከላከል እንቅስቃሴያቸው ሙሉ ጨዋታውን በጥሩ የአካል ብቃት ዝግጁነት ከመጨረሳቸው ጋር ሲሆን በቀጣይ መርሀ ግብሮች ተፅዕኖ ፈጣሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነበር። አሁን ላይ አስፈላጊነታቸው በዓለም እግር ኳስ ውስጥ እየጎላ የመጣው የቦታው ተሰላፊዎች ብዛት እና ጥራት በሊጉ ውስጥ መበራከት እንደሀገርም ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ በመሆኑ በቀጣይ ሳምንታት የእነዚህን ተጫዋቾች ወጥ ብቃት በአንክሮ እንድንከታተል ያደርገናል።
የተከላካይ አማካዮች ጥምረት…
ከተከላካይ መስመራቸው ፊት ሁለት አማካዮችን የሚያጣምሩ ቡድኖች የተጋጣሚዎቻቸውን የማጥቃት ሒደት በቀላሉ ሲቆጣጠሩ የነበሩበትን የጨዋታ ሳምንት መመልከት ችለናል። በፋሲል ከተማ የይሁን እንዳሻው እና ሀብታሙ ተከስተ ፣ በአዳማ ከተማ የደሳለኝ ደባሽ እና ዘሪሁን ብርሀኑ እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ የፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ሳምሶን ጥላሁን ጥምረቶች በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ነበሩ። እነዚህ ጥምረቶች በቅደም ተከተል በተቃራኒ ቡድን በከነዓን ማርክነህ፣ ሱራፌል ዓወል እና ዳዊት ተፈራ የሚመሩ የአማካይ ክፍሎችን ተጋፍጠዋል። ምንም እንኳን የተጋጣሚዎቻቸው አቀራረብ ላይ የማጥቃት ስትራቴጂዎች አማራጮች ሰፊ ያልነበሩ ቢሆንም በመሀከላቸው የነበረው መናበብ ግን በቀጥታም ሆነ በጎንዮሽ ይሰነዘሩ የነበሩ ጥቃቶችን እንዲመክቱ ለማስቻሉ መናገር ይቻላል። በተለይም የፍቅረሚካኤል እና የሳምሶን መናበብ ሁለቱም ሰፊ የሜዳ ክልልን ሳይሸፍኑ በተቆጠበ ጉልበት የሚፈለገውን ሽፋን ለተከላካይ መስመሩ እንዲሰጡ ሲረዳቸው ተስተውሏል።
ለኳስ ቁጥጥር ያደሉ ቡድኖች ፈተና…
በሳምንቱ ከተቆጠሩት ግቦች አብዛኞቹ በፈጣን ሽግግር፣ በተከላካዮች ስህተት መነሻነት እና በቆሙ ኳሶች የተቆጠሩ ናቸው። ቡድኖች ወደ ሜዳ ይዘውት በሚገቡት የጨዋታ ሀሳብ መነሻነት ግቦችን አስቆጥረው ጨዋታዎችን በወጥነት ማሸነፍ ካልቻሉ ደግሞ አጨዋወታቸው ስኬትን እያመጣላቸው ነው ማለት ያስቸግራል። በዚህ መንገድ መጠኑ ይለያይ እንጂ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለመያዝ ፍላጎቱ ላላቸው ቡድኖች ሳምንቱ ጥሩ አልነበረም። በዚህ ረገድ የተሻሉ ዕድሎችን መፍጠር የቻለው እና ግቦችንም ያስቆጠረው ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል። ሆኖም ቡድኑ በወልቂጤ ሜዳ ላይ ከደረሰ በኋላ የተሻለ ክፍተት የመፍጠር አቅም እንደታየበት የፈጠራቸው ዕድሎች ቢመሰክሩም ከኋላ ኳስ ሲጀምር የሚደረግበትን ጫና መቋቋም ላይ ግን ብዙ እንደሚቀረው ታይቷል። ይህም በቅንጅት ደረጃ የተዋጣለት ባልነበረው ይልቁኑም በግል የተጫዋቾች ሩጫ ላይ በተመሰረተው የወልቂጤ ጫና የመፍጠር ሒደት ተፈትኖ የታየ ነው። በመሆኑም ፈተናው ከዚህ ላቅ ሲል የቡድኑ የኋላ መስመር ስህተቶች እንዳይበዙ ያሰጋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡናም በተመሳሳይ መልኩ በቅብብሎች አማካይነት በተጋጣሚ የኋላ መስመር ክፍተቶችን ለማግኘት ብዙ የለፉ ቡድኖች ነበሩ። የፈጠሯቸው የመጨረሻ ዕድሎች ግን በቁጥር ጥቂት ነበሩ። የመስመር ተከላካዮቻቸው የማጥቃት ተሳትፎ በሚፈለገው መጠን አለመሆን ከመስመር የሚነሱ አጥቂዎቻቸው ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት ተጋጣሚን የማስከፈት አቅማቸው መድከሙ ግልፅ አጋጣሚዎችን ላለመፍጠራቸው እንደምክንያትነት ሊነሱ ይችላሉ። ከዚያ ውጪ ግን ሁለቱም አብዛኛውን የፈጠራ እና የመጨረሻ ኳስ የማድረስን ነገር ከከነዓን ማርክነህ እና ከዳዊት ተፈራ መጠበቃቸው ሌላኛው ምክንያት የሆነ ይመስላል። ተጋጣሚዎቻቸው በሁለቱ ተጫዋቾች ላይ የፈጠሩት ጫናም ማጥቃቱን ይበልጥ ሲያዳክመው ታይቷል።
የቡድኖቹ አሰልጣኞች ከአማካይ ክፍላቸው በዕድሎች የታጀበ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማሳካት የሚረዳ እንቅስቃሴ እንዳላገኙ ከሚያሳዩ ነገሮች አንዱ ቅያሪዎቻቸው ነበሩ። በደስታ ደሙ ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና ከነዓን ማርክነህ የአማካይ ክፍል ጥምረት ጨዋታውን የጀመረው ጊዮርጊስ ጨዋታው ሲገባደድ ሦስቱንም ተክቷቸዋል፤ ደስታ የሚና ለውጥ አድርጎ ወደ መስመር ተከላካይነት ሲሄድ ሁለቱ አማካዮች ተቀይረው ወጥተዋል። በተመሳሳይ ሲዳማ ቡና ግርማ በቀለ ፣ ዳዊት ተፈራ እና አበባየሁ ዮሐንስን ተጠቅሞ ጨዋታውን ቢጀምርም ግርማ ወደ መሐል ተከላካይነት ሲመለስ አበባየውን ቀይሮታል። ይህ ሁኔታ ጨዋታውን በቁጥር ብልጫ ታግዞ ያሸንፍ እንጂ በአዳማ ከተማም ታይቷል። በቀይ ካርድ ምክንያት በቁጥር አንሰውም ቢሆን በተወሰኑ የጨዋታው ክፍሎች ላይ ጅማ አባ ጅፋሮች የኳስ ቀጥጥሩ ላይ ተሽለው ይታዩ ነበር። በዚህም ምክንያት ይመስላል አምስት አማካዮችን የተጠቀመው አዳማም እንዲሁ ሦስቱን ቅያሪዎቹን በሙሉ ያደረገው አማካይ ክፍሉ ላይ ነበር። የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ መሰረት የሚያደርጉ ቡድኖች አማካይ ክፍላቸው ላይ የሚኖረው የግልም ሆነ የጋራ የጥራት ደረጃ ከፍ ማለት ያለበት መሆኑ የግድ ነውና ቡድኖቹ በቀጣይ ሳምንታት ምን ዓይነት ለውጥ ይዘው እንደሚመጡ የሚጠበቅ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ