የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ተካፋዩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አስራ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሁለት ነባሮችን ውልም አራዝሟል፡፡
በቅርቡ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናን ዋና አሰልጣኝ አድርገው የቀጠሩት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጥቂት የዝግጅት ጊዜን አዲስ አበባ ላይ በመስራት ከሰነበቱ በኋላ ትላንት ረፋድ ወደ ሀዋሳ አምርተዋል፡፡ ክለቡም ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም ለመመለስ ውል በክለቡ በነበራቸው ስድስት ተጫዋቾች ላይ አስራ አራት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ የአምበሉ አዲስ ነጋሽ እና ቢኒያም ትዕዛዙን ኮንትራት ደግሞ ለተጨማሪ ዓመት አራዝመዋል፡፡
ክለቡን ከተቀላቀሉ ተጫዋቾች መካከል የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር ግብ ጠባቂ ዘሪሁን ታደለ እና የቀድሞ የሰበታ ግብ ጠባቂ ቢኒያም ታከለን ከኢትዮጵያ መድን ሲቀላቀሉ በወልዋሎ እና መከላከያ ሲጫወት የምናውቀው ዓለምነህ ግርማ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በአዳማ እንዲሁም አምና ኢትዮጵያ ቡናን ቢቀላቀልም በጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ያልቻለው አንዳርጋቸው ይላቅ፣ ፍራኦል መንግሥቱ ከሀድያ ሆሳዕና፣ ብሩክ ጌታቸው ከአዲስ አበባ ከተማ በተከላካይነት ክለቡን የተቀላቀሉ ናቸው።
የቀድሞው የኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ እና ዐምና በሰበታ ከተማ በመጫወት አሳልፎ በስምምነት ሰሞኑን የተለያየው ሳሙኤል ታዬን ጨምሮ፣ አቤል ታሪኩ ከሰበታ ከተማ፣ ሀብታሙ ጥላሁን ከመከላከያ፣ እንዳለ ዘውገ ከሰበታ ከተማ በአማካይ ስፍራ የሚጫወቱ አዲሶቹ ፈራሚዎች ናቸው።
በአጥቂ ሥፍራ የቀድሞው የኒያላ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ዳሽን እንዲሁም ከሰሞኑ ከሀዋሳ ከተማ ጋር የአንድ ዓመት ውል እየቀረው በስምምነት የተለያየው የተሻ ግዛው፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መከላከያ እንዲሁም በደቡብ ፖሊስ የምናውቀው መስፍን ኪዳኔ፣ በፋሲል ከነማ እና ያለፉትን ሁለት ዓመታት በጅማ አባጅፋር በመጫወት ያሳለፈው ኤርሚያስ ኃይሉ እንዲሁም መከላከያን ለቆ ዓምና በመድን ቆይታ የነበረው አቅሌሲያስ ግርማ የኢትዮ ኤሌክትሪክን ስብስብ መቀላቀል የቻሉ ልምድ ያላቸው አዳዲስ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ